የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ጥሏል፡፡ በዳሽን እና ኤሌክትሪክ መካከል ላለመውረድ የሚደረገው ፍጥጫም እስከመጨረሻው ሳምንት ዘልቋል፡፡
09:00 ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለግብ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ ጨዋታው የተቀዛቀዘና እጅግ ጥቂት የግብ እድሎች የተፈጠሩበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡
ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ደደቢት 2-1 አሸንፏል፡፡ ደደቢት በዳዊት ፍቃዱ ግብ ቀዳሚ መሆን ሲችል በላይ አባይነህ ባለሜዳዎቹን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ የሰማያዊዎቹን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ናይጄርዊው ሳሙኤል ሳኑሚ ነው፡፡
ወደ ሆሳዕና ያቀናው ኢትዮጽያ ቡና ወራጁ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 አሸንፏል፡፡ ያቡን ዊልያም እና ሳዲቅ ሴቾ የቡናን የድል ግብ ከመረብ ሲያሳርፍ ዱላ ሙላቱ የሀዲያ ሆሳዕናን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ወደ ይርጋለም የተጓዘው አርባምንጭ ከተማ ካለ ግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ይህ ውጤት ለአርባምንጭ ከተማ ከመውረድ ስጋት ነጻ ያወጣ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ኤሌክትሪክ ከቦዲቲ 1 ነጥብ ይዞ ተመልሷል፡፡ ወላይታ ድቻን የገጠመው ኤሌክትሪክ ካለ ግብ 0-0 ማጠናቀቁን ተከትሎ ከዳሽን ጋር ያለው የነጥብ ልዩነቱን ማስጠበቅ ችሏል፡፡
ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ዳሽን ቢራን አስተናግዶ 2-2 ተለያይቷል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች በዮሃንስ ሰገቦ እና ፍርድአወቅ ሲሳይ ግቦች 2-0 ሲመሩ ቆይተው ኤዶም ሆሶዎሮቪ እና የተሻ ግዛው የጎንደሩን ክለብ አቻ አድርገዋል፡፡
በጨዋታው ጫማውን ለመስቀል ከውሳኔ ላይ የደረሰው ሙሉጌታ ምህረት ከደጋፊዎች ስጦታ የተበረከተለት ሲሆን ፍርዳወቅ ሲሳይ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ለሙሉጌታ ያለውን ክብር ገልጿል፡፡
ውጤቱ ዳሽን ቢራ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ እንዲቆይ ያስገደደው ሲሆን የመጨረሻውን ጨዋታ አሸንፎ የኤሌክትሪክን ውጤት የመጠበቅ ግዴታ ውስጥ ገብቷል፡፡
11:30 ላይ ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ጋር አቻ ተለያይቷል፡፡ በጨዋታው መጀመርያ የመከላከያ ተጫዋቾች የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን በክብር በማጀብ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
መሃመድ ናስር በ9ኛው ደቂቃ የኦዶንካራን ስህተት ተጠቅሞ ባስቆጠረው ግብ መከላከያ እስከ ጨዋታው መገባደጃ ድረስ መምራት ቢችልም ተቀይሮ የገባው ዳዋ ሁቴሳ በ90+4ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሽንፈት የታደገች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ግቧ የተቆጠረችው የተጨመረው ደቂቃ ካለፈ በኋላ ነው በሚል የመከላከያ ቡድን አባላት ከዳኞች ጋር ውዝግብ ሲፈጥሩ ታይቷል፡፡
ሊጉ በመጪው ማክሰኞ እና ረቡዕ በሚደረጉ ጨዋታዎች ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ ሻምፒዮኑ እና አንደኛው ወራጅ ቡድን ቀደም ብለው በመታወቃቸው በመጨመረሻው ሳምንት ጨዋታዎች የሚጠበቀው ሀዲያ ሆሳዕናን ተከትሎ ማን ወደ ከፍተኛ ሊግ ይወርዳል የሚለው ይሆናል፡፡ ዳሽን 25 ፣ ኤሌክትሪክ 27 ነጥብ ይዘው ላለመውረድ ተፋጠዋል፡፡
ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ታፈሰ ተስፋዬ በ14 ግቦች ሲመራ ዳዊት ፍቃዱ በ12 ይከተላል፡፡
የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች
ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2008
08፡00 ዳሽን ቢራ ከ ሲዳማ ቡና (አዳማ)
09፡00 ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (አበበ ቢቂላ ስታድየም)
09፡00 አርባምንጭ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ (አርባምንጭ)
10፡00 አዳማ ከተማ ከ መከላከያ (አዳማ)
11፡30 ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ (አአ ስታድየም)
ረቡዕ ሰኔ 22 ቀን 2008
08፡30 ደደቢት ከ ሀዲያ ሆሳዕና (አአ ስታድየም)
10፡30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ (አአ ስታድየም)