በ2018 ሩሲያ ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የተፋጠጡት 20 የአፍሪካ ሃገራት ዛሬ በግብፅ መዲና ካይሮ በሚገኘው ማሮይት ሆቴል የምድብ ድልድላቸውን አውቀዋል፡፡ ምድብ ሁለት ከወዲሁ የሞት ምድብ ስያሜን ሲያገኝ ጋናና ግብፅ ዳግም አንድ ላይ ተደልድለዋል፡፡
በምድብ አንድ የሰሜን አፍሪካዎቹ ቱኒዚያ እና ሊቢያ፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ እንዲሁም በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው መጥፎ ውጤት ያስመዘገበችው ጊኒን ይዟል፡፡
ምደብ ሁለት አልጄሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ካሜሮን እና ዛምቢያን ያጣመረ ሲሆን ከዛምቢያ በስተቀር የተቀሩት ሶስቱ ሃገራት አፍሪካን ወክለው ብራዚል ባስተገደችው የ2014ቱ የአለም ዋንጫ ተካፋይ ነበሩ፡፡
ሞሮኮ ከ1998 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ዓለም ዋንጫው ለማለፍ በምድብ ሶስት ከኮትዲቯር፣ ማሊ እና ጋቦን ብርቱ ፉክክር ይጠብቃታል፡፡ የአትላስ አናብስቶቹ አሰልጣኝ ሆርቬ ሬናርድ በ2015 የአፍሪካ ቻምፒዮን ካደረጋቸው ከዝሆኖቹ ጋር ተፏጧል፡፡
በምድብ አራት ሃያልነቷን እያሳየች የመጣችው ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ደሴቲቷ ኬፕ ቬርድ እና ከ2014ቱ አለም ዋንጫ በአልጄሪያ ተሸንፋ የቀረችው ቡርኪና ፋሶ ይገኛሉ፡፡
በምድብ አምስት ፈርኦኖቹ ከጋና ዳግም ሲገኛኙ ብቸኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ዩጋንዳ እና ኮንጎ ብራዛቪልም በምድቡ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጋና ግብፅን 7-3 ሰፊ በሆነ የድምር ውጤት መርታቷ ይታወሳል፡፡ ኮንጎ ብራዛቪል ኢትዮጵያ 6-4 በማሸነፍ ከዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ያሰናከለች ሲሆን ዩጋንዳ በማጣሪያው የምትገኝ ብቸኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ሃገር ነቸ፡፡
የምድብ ማጣሪያው የወጣበት ቋት ፊፋ ለካፍ ባሳወቀው የተለየ የሃገራት ደረጃ መሰረት ሲሆን አልጄሪያ፣ ኮትዲቯር፣ ጋና፣ ሴኔጋል እና ቱኒዚያ በቋት 1 የተገኙ ሃገራት ናቸው፡፡ ግብፅ የተለየ የሃገራት ደረጃ ላይ ቅሬታዋን ብታቀርብም የተለወጠው ደረጃ ምንም ልዩነት አልፈጠረም፡፡
የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ በፈረንጆቹ ጥቅምት ወር የሚጀመር ሲሆን ከአምስቱ ምድቦች አንደኛ የሚወጡት አምስት ሃገራት አፍሪካ በሩሲያው የዓለም ዋንጫ የሚወክሉ ይሆናል፡፡
የፎቶዎች ምንጭ፡ Dr. Hosam and CAF