የጎ-ቴዲ ፉትሳል ዋንጫ በቲጂ እና ጓደኞቹ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌደሬሽን ከጎ-ቴዲ ስፖርት ጋር በመተባበር ለ15 ቀናት በወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ሲከናወን የነበረው የ2008 ፉትሳል ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

ትላንት በተደረጉ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ጂኬ ኢትዮጵያ ሊና ሆቴልን 5ለ3 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ለአሸናፊው ቡድን ቢኒያም ወርቁ (2) ፣ ኤፍሬም አሻግሬ ፣ ሄኖክ ሩጋ እና አዳም ግሌዘር ሲያስቆጥሩ ለተሸናፊው ቡድን ተስፋዬ አበራ(2) እና ቅዱስ አስመላሽ ማስቆጠር ችለዋል።

ቀጣይ በተደረገው እና ጥሩ የጨዋታ ፉክክር በተስተዋለበት ጨዋታ ቲጂና ጓደኞቹ ኢኤስኤፍን 8-7 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለፍጻሜው ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ለቲጂና ጓደኞቹ መሃመድ ወርቁ (2) ፣ በልሁ ሀይሌ ፣ ሰለሞን ፈለቀ ፣ ሲሳይ ነጋሽ ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ (3) ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ለኢኤስኤፍ ከመሸነፍ ያላዳናቸውን ጎሎች ቢኒያም አሰፋ(4) ኤልያስ በሃይሉ ሲሳይ ነጋሽ [በራሱ ላይ] እንዲሁም ሮቤል ሰለሞን አስቆጥረዋል።

PicsArt_1466958528291

በዛሬው የፍጻሜ እና የደረጃ ጨዋታዎች ይደረጋሉ ተብሎ መርሃ ግብር ቢወጣለትም የተከናወነው ጨዋታ ግን የፍጻሜው ጨዋታ ብቻ ነበር። ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የኢኤስኤፍ እና የሊና ሆቴል ጨዋታ ኢኤስኤፎች ባለመምጣታቸው ምክንያት ፎርፌ ለሊና ሆቴል ተሰጥቷል።

ለዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ጂኬ ኢትዮጵያ እና ቲጂ እና ጓደኞቹ ጨዋታቸውን ከመጀመራቸው በፊት የእለቱ የክብር እንግዶች ለነበሩት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን በሻ ጨምሮ ለሌሎች እንግዶች ሰላምታ በመስጠት ነበር ጨዋታው የጀመረው።

በጨዋታው ሁለቱ የጨዋታ ክፍለ ጊዜዎች ፍጹም የተለያዩ እንደነበር በተስተዋለበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ሁለቱ ቡድኖች ተመጣጣኝ የጨዋታ ፉክክር አሳይተው ነበር። በጨዋታው ላይ እንደ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ኤልያስ ማሞ የዳኛን ውሳኔ በመቃወም ከእለቱ  ዳኞች ጋር በፈጠረው ሰጣገባ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል። ከኤልያስ ማሞ መውጣት በኃላ ጫና የበዛባቸው የጂኬ ተጨዋቾች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ተወስዶባቸው እንደነበር አስተውለናል።

በአጠቃላይ ጨዋታው በቲጂና ጓደኞቹ 9ለ5 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ለቲጂና ጓደኞቹ ለሚ ኢታና(3) ሲሳይ ነጋሽ (2) መሃመድ ወርቁ (4) ግቦችን ሲያስቆጥሩ ለጂኬ ኢትዮጽያ ኤልያስ ማሞ(2) ኤፍሬም አሻግሬ (2) እንዲሁም ቢኒያም ወርቁ ከሽንፈት ያላዳነቻቸውን ግቦች አስቆጥረዋል።

PicsArt_1466958425797

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተከናወነው ሽልማት ስነ-ስርዓት በውድድሩ ሶስተኛ ሆኖ ላጠናቀቀው ሊና ሆቴል የነሃስ ሜዳሊያ ሲሰጥ በፍጻሜው ተሸንፎ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ጂኬ ኢትዮጽያ የብር ሜዳሊያ እና የ2500 ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ውድድሩን በአንደኝነት ያጠናቀቀው ቲጂና ጓደኞቹ የወርቅ ሜዳሊያ ፣ ዋንጫ እና የ7500 ብር ተሸላሚ መሆን ችለዋል፡፡

በውድድሩ 22 ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ መሆን የቻለው ቢኒያም አሰፋ ከኢኤስኤፍ ሲሆን የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች መሃመድ ወርቁ ከቲጂና ጓደኞቹ በመሆን የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ወስደዋል።

ለ15 ቀናት በቆየው በዚህ ውድድር በአጠቃላይ 15 ጨዋታዎች ሲደረጉ 234 ያክል ግቦች ከመረብ ላይ አርፈዋል። በአማካይ በጨዋታ 15.6 ያክል ግቦች ሲቆጠሩ ከተደረጉት ጨዋታዎች ከፍተኛ

ግቦችን ያስቆጠረው ቡድን ቲጂና ጓደኞቹ በ47 ግቦች ነው። 4 የቢጫ ካርድ እና 4 የቀይ ካርዶች በተስተናገዱበት የ2008 የፉትሳል ውድድር ዝግጅቱ በታቀደለት መሰረት በተሳካ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፉትሳል ኮሚቴ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፉትሳል ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዮናስ ሃጎስ ውድድሩ ላይ ለተሳተፉ የቡድን አባላት ለዳኞች ለተመልካቾች ለወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አመራሮች እና ሰራተኞች እንዲሁም ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል። ውድድሩን ሙሉ ለሙሉ ስፖንሰር ላደረገው ጎ-ቴዲ ስፖርት ከፍተኛ ምስጋናም ጨምረው አቅርበዋል።

አቶ ዮናስ ሃጎስ በዝግጅቱ ላይ ለተፈጠሩ የሰዓት መዘግየቶች የዳኝነት ጉድለቶች እና ለሌሎች እንከኖች ይቅርታ ጠይቀው ወደፊት በሚኖሩ ውድድሮችም ላይ እነዚህን ስህተቶች ለመቅረፍ ጠንካራ ስራዎች እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *