የአልጄሪያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከክርስቲያን ጎርከፍ ስንብት በኃላ አዲሱን አሰልጣኝ ዛሬ በይፋ አሳውቋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ በኃላ ራሳቸውን ከበረሃ ቀበሮዎቹ አሰልጣኝነታቸው ያነሱት ጎርከፍን የተኩት ሰርቢያዊው ሚሎቫን ራይቫክ ናቸው፡፡
በጊዜያዊ አሰልጣኞቹ ነቢል ነግሂዝ እና ያዚድ መንሱሪ እየተመራ ሲሸልስን ቪክቶሪያ ላይ 2-0 በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያለፈ ሲሆን አዲሱ አሰልጣኝ ራይቫክ አልጄሪያን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እና በመጪው ዓመት ጥር ላይ በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ ግዴታ አለባቸው፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አልጄሪያ ከወዲሁ የሞት ምድብ ከተባለው ምድብ ሁለት ከናይጄሪያ፣ ካሜሮን እና ዛምቢያ ተደልድላለች፡፡
ጋናን ከክላውድ ለርዋ በኃላ ያሰለጠኑት ራይቫክ በ2010 የዓለም ዋንጫ ብላክ ስታርስን ሩብ ፍፃሜ ያበቁ ሲሆን በመካከለኛው ምስራቅ በሳዑዲ አረቢያ እና ካታር እንዲሁም በሩቅ ምስራቅ ቻይና የአሰልጣኝነት ህይወትን መርተዋል፡፡ ወደ አፍሪካ የመመለስ ብርቱ ፍላጎት የነበራቸው ራይቫክ ቤኒን እና ካሜሮንን ለማሰልጠን ከጫፍ ደርሰው ነበር፡፡
በምድብ 10 በ13 ነጥብ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፏን ያረጋገጠቸው አልጄሪያ በአዲሱ አሰልጣኝ ራይቫክ እየተመራች ከሌሶቶ ጋር የምታደርግ ይሆናል፡፡
የዚሁ ምድብ ሃገራት በሙሉ በማጣሪያው ወቅት የአሰልጣኝ ሹም ሽር ያደረጉ ሲሆን ሲሸልስ ብሩኖ ሳኢንዲኒ፣ ራልፍ ጂያን ሉዊ እና ኡልሪክ ማትዮትን በማጣሪያው ብቻ ስትጠቀም፤ ሌሶቶ ሴፊፊ ማቴቴን በሞሰስ ማሊሂ ቀይራለች እንዲሁም ኢትዮጵያ ዮሃንስ ሳህሌን በገብረመድህን ሃይሌ ተክታለች፡፡