ፕሪሚየር ሊግ ፡ የኤሌክትሪክ አና ዳሽን ቢራ አሰልጣኞች ከመውረድ እንደሚተርፉ ተማምነዋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ነገ ላለመውረድ የሚደረገውን ትንቅንቅ እልባት ያበጅለታል፡፡

በሁለት ነጥብ ልዩነት 12ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ ተከታትለው የተቀመጡት ኤሌክትሪክ እና ዳሽን ቢራ ነገ በሚያደርጓቸው የመጨረሻ ጨዋታዎች የፕሪሚየር ሊግ ቆይታቸውን ይወስናሉ፡፡

አአ ስታድየም ላይ ንግድ ባንክን የሚገጥመው ኤሌክትሪክ የመትረፍ ሰፊውን እድል ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ቀዮቹ ካሸነፉ የዳሽንን ውጤት ሳይጠብቁ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየታቸውን የሚያረጋግጡ ሲሆን አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩም ክለቡን ለማትረፍ መክፈል ያለባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ እንደሚከፍሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

” የመጨረሻው ጨዋታ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ቡድን በዚህ ደረጃ መጫወት አልነበረበትም፡፡ እንደሜዳ ላይ እንቅስቃሴያችንና እንደያዝነው የተጨዋች ጥራት አሁን ያለንበት ነጥብ አይገልፀውም፡፡ ለዚህ ያበቁን የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ፤ ነገር ግን ኤሌክትሪክ በምንም ተአምር አይወርድም፡፡ የሚከፈለውን መሰዋአትነት ከፍለን ይህን ታሪካዊ ክለብ በዚህ ሊግ ላይ እናቆየዋለን ብዬ አምናለው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

PicsArt_1467054778138

ዳሽን ቢራ የማለፍ ተስፋው በኤሌክትሪክ ሽንፈት ወይም አቻ ውጤት ላይ ተንጠልጥሎ ሲዳማ ቡናን አዳማ ላይ ያስተናግዳል፡፡

ቡድኑን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የተረከቡት አሰልጣኝ ተገኝ እቁባይ ግን ቡድናቸው እንደሚተርፍ ተማምነዋል፡፡

” በተጫዋቾቹ በኩል ያለው ፍላጎትና ተነሳሽነት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ካደረግናቸው ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻልን ነው፡፡ በመጨረሻ ጨዋታችን ሲዳማ ቡናን አሸንፈን የሚቀጥለው አመት የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ እንደምንሆን በርግጠኝነት መናገር እችላለው፡፡ በሚቀጥለው አመትም ጥሩ ተፎካካሪ ሆነን እንቀርባለን፡፡ “ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ደረጃ

12. ኤሌክትሪክ 25 (-12) 27
13. ዳሽን ቢራ 25 (-7) 25

ጨዋታዎች

08:00 ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (አአ ስታድየም)

08:00 ዳሽን ቢራ ከ ሲዳማ ቡና (አዳማ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *