የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ማዳጋስካር ለምታስተናግደው የ2017 የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ለማለፍ ከግብጽ ጋር በሀምሌ ወር መጨረሻ የማጣርያ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑን በአሰልጣኝነት የተረከቡት አጥናፉ አለሙ ፣ ረዳታቸው አሰልጣኝ ቅጣው ታደሰ እንዲሁም የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ አዳሙ ኑመሮ ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ የተጫዋቾች ምርጫ ላይ ተጠምደው የቆዩ ሲሆን በሂደቱም ከ100 በላይ ተጫዋቾች ታይተዋል፡፡
ምርጫው ሁለቱን ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ዞኖች የሸፈነና በክልሎች በመዟዟር ለመመልመል ጥረት እንደተደረገ ተገልጿል፡፡
በሊጉ የሚጫወቱ አቅም ያላቸው አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች በMRI ምርመራ መውደቃቸው ምልመላውን ፈታኝ እንዳደረገው አሰልጣኝ አጥናፉ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ክለቦችም ተጫዋቾትን ሲመለምሉ እንደ ሀገር ሊያስቡበት እንደሚገባ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰአት 26 ተጫዋቾች የተለዩ ሲሆን ከሐምሌ መጀመርያ አንስቶ በሀዋሳ አልያም ባህርዳር ዝግጅታቸውን ለመጀመር እንዳሰቡ ተናግረዋል፡፡ በዝግጅቱ ወቅትም 3 ተጫዋቾች እንደሚቀነሱ ታውቋል፡፡
አሰልጣኝ አጥናፉ በዝግጅት ወቅት በተመረጡት ልጆች ላይ ከፍተኛ የማብቃት የቅንጅት ስራ እንደሚሰራ እና ተስፋ ሰጪ ውጤት ለማሳየት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ፌዴሬሽኑ በሁሉም ረገድ ድጋፍ ማድረጉ ስራቸውን እንዳቀለለውና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የተመረጡ 26 ተጫዋቾች ዝርዝር
ኦኛ ኦሜኛ ፣ እሸቱ ተሾመ ፣ ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ረመዳን የሱፍ መሃመድ ፣ እሱባለው ጌታቸው ፣ ማትያስ ወልደአረጋዊ ፣ ሚኪያስ መኮንን ፣ አቡበከር ናስር ፣ ዳዊት ሳህሌ ፣ ጫላ ተሸታ ፣ እዮብ አለማየሁ ፣ ዳግማዊ አርአያ አምበፍርድ ፣ ሰለሞን ሙላው ፣ መሃመድ ሙስጠፋ ፣ መድህን ካህሳይ ፣ ሳሙኤል ተስፋዬ ፣ አሸናፊ ማስረሻ ፣ አማኑኤል አዲሱ ፣ ሉክ ፖውልን ፣ ሀቢብ ከተማ ፣ አላዛር ሽመልስ ፣ ጌታሰጠኝ ሸዋ ፣ አብዱልሽኩር ሀዲ ኡመር ፣ አክሊሉ ለአሙ ፣ ኢዩኤል መስፍን