በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 33ኛ ሳምንት የሁለቱ ኢትዮጵያዊያንን ክለቦች ሲያገኛኝ ኢኤንፒፒአይ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡
አጥቂው አህመድ ጋፍር ፔትሮጀት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ያለመግባትን ተከትሎ በፊት መስመር የተሰለፈው ሽመልስ በቀለ ሙሉ 90 ደቂቃ መጫወት ሲችል ከኢኤንፒፒአይ መውጫውን በር እየፈለገ የሚገኘው ኡመድ ኡኩሪ በቡድኑ ውስጥ አልተካተተም፡፡
ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ የቀረው የግብፅ ፕሪምየር ሊግን አል አሃሊ ተከታዩን ዛማሌክን በሰባት ነጥብ በመብለጥ ሻምፒዮን የሆነ ሲሆን በፔትሮስፖርት ስታዲየም ፔትሮጀትን ያስተናገደው ኢኤንፒፒአይ ድል ቀንቶታል፡፡
ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው ፔትሮጀቶች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ የተሻሉ የነበረ ቢሆንም ከሽንፈት ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ በተለይ ሽመልስ በ33ኛው ደቂቃ ንፁህ የግብ ማግባት አጋጣሚ ቢያገኝም የኢኤንፒፒአዩ ግብ ጠባቂ አሊ ሎትፊ አምክኖበታል፡፡
የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ አምር ኤል ሃላዋኒ የኢኤንፒፒአይን የድል ግብ በቅጣት ምት አስገኝቷል፡፡ ውጤቱን ለመቀልበስ በሁለተኛው አጋማሽ ሙከራ ያደረጉት ፔትሮጀቶች ጠንካራውን የኢኤንፒፒአይ የተከላካይ መስመር መስበር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በ77ኛው ደቂቃ ሽመልስ በአክሮባቲክ ምት ደረገው ሙከራ አደጋ ሳይፈጥር ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡
ድሉን ተከትሎ ኢኤንፒፒአይ በ44 ነጥብ 10ኛ ሲሆን ተሸናፊው ፔትሮጀት በ43 ነጥብ 11ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡
ሊጉን ሻምፒዮኑ አል አሃሊ በ74 ነጥብ ሲመራ ነጥብ ሲመራ ዛማሌክ እና አል መስሪ ተከታዮቹን ደረጃዎች በ67 እና 53 ነጥብ ይዘዋል፡፡ ኢቲሃድ ኤል ሾርታ፣ ሃራስ ኤል ሆዶድ እና ጋዛል ኤል ማሃላ ከሊጉ መውረዳቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ፔትሮጀት በሜዳው ወራጁን ኢቲሃድ ኤል ሾርታን ሲያስተናግድ፤ ኢኤንፒፒአይ ፋዩም ላይ ምስር ኤል ማቃሳን ይገጥማል፡፡
የኮከብ ግብ አግቢነቱን ሆሳም ፓውሎ ከሰሞሃ በ16 ግቦች ሲመራ አህመድ ራዉፍ ከአል መስሪ እና ማርዋን ሞሰን ከኢስማኤሊ በ13 ግቦች ይከተላሉ፡፡