ኮንፌድሬሽን ካፕ፡ ቲፒ ማዜምቤ እና ካውካብ በአሸናፊነታቸው ቀጥለዋል

በኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ ቲፒ ማዜምቤ እና ካውካብ ማራካሽ ተጋጣሚዎቻቸውን በመረታት የ100% ማሸነፍ ሪከርዳቸውን አስጠብቀዋል፡፡ ቲፒ ማዜምቤም በ2016 የውድድር ዓመት በካፍ ውድድሮች ከሜዳው ውጪ ለመጀመሪያ ግዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡

ዳሬ ሰላም ላይ በብዙ ሺህ ተመልካች ፊት ያንግ አፍሪካንስን የገጠመው ቲፒ ማዜምቤ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ የያንጋ ቀንደኛ ተቀናቃኝ የሆነው ሲምባ ክለብ ደጋፊዎች ለማዜምቤ ድጋፋቸው የሰጡ ሲሆን ያንጋ ደጋፊዎቹን በነፃ ወደ ስታዲየም እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ከጨዋታው መጀመር አራት ሰዓታት በፊት ቀደም ብሎ የሞላው ስታዲየም አስደናቂ ድባብ ታይቶበታል፡፡

PicsArt_1467189263116

PicsArt_1467189243118

የሉቡምባሺውን ክለብ የድል ግብ ማርቬል ቦፔ ቦኮንዲ በ75ኛው ደቂቃ ማስገኝት ችሏል፡፡ ሽንፈቱን ተከትሎ ያንጋ ያለምንም ነጥብ የምድቡ ግርጌ ላይ ሲገኘ ማዜምቤ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያደርገውን ግስጋሴ አሳምሯል፡፡

በምድብ ሁለት ምሽት ላይ በገለልተኛ ሜዳ የተገናኙት አል አሃሊ ትሪፖሊ እና ካውካብ ማራካሽ ነበሩ፡፡ የሰሜን አፍሪካውን ደርቢ የሞሮኮው ክለብ በድል ተውጥቷል፡፡ ካውካብ ከአራት ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በኃላ በኮንፌድሬሽን ካፑ ማሸነፍ ችሏል፡፡ መሃመድ ኤል ፋኪህ በ34ኛው ደቂቃ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ቀይሮ ካውካብን መሪ ሲያደርግ ከአራት ደቂቃ በኃላ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ መሃመድ አል ጋኖዲ አሃሊ ትሪፖሊን አቻ አድርጓል፡፡ በ64ኛው ደቂቃ ብራዚሊያዊው ጄፈርሰን ሉዊዝ የማራካሹን ክለብ የድል ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ካውካብ ማራካሽ ምድብ ሁለትን በ6 ነጥብ ሲመራ ተሸናፊው አሃሊ ትሪፖሊ የምድቡ ግርጌን ይዟል፡፡

PicsArt_1467189213599

የምድብ ጨዋታዎቹ ዛሬም ሲቀጥሉ በምድብ አንድ ሚዲአማ ኤምኦ ቤጃያን ያስተናግዳል፡፡ ቤጃያ በመክፈቻው ጨዋታ ያንጋን ያሸነ ሲሆን ሚዲአማ በቲፒ ማዜምቤ ተሸንፏል፡፡ እስካሁን በሜዳው ያደረጋቸውን የኮንፌድሬሽን ካፕ ጨዋታዎች 2-0 በሆነ ውጤት ያጠናቀቀው ሚዲአማ በሜዳው ያለው ጥሩ ሪከርድ ላይ ተማምኗል፡፡ በዘንድሮው የውድድር አመት በአሀጉሪቱ ውድድች ላይ ጠንካራነቱን ያስመሰከረው ቤጃያ በመሃመድ ዋሊዩ ንዶዬ መሪነት ሚዲአማን ይፈትናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በምድብ ሁለት የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ሶስ ቱኒዚያ ሲደረግ የወቅቱ የቱኒዚያ ሻምፒዮን እና የ2015 የካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊው ኤቷል ደ ሳህል ከሞሮኮው ሻምፒዮን ፉስ ራባት ከባድ የሆነ የሰሜን አፍሪካ ደርቢ ያደርጋሉ፡፡ ኤቷል በምድብ መክፈቻ ጨዋታ በካውካብ ማራካሽ 2-1 የተሸነፊ ሲሆን ፉስ ራባት አሃሊ ትሪፖሊን 1-0 መርታት ችሏል፡፡ ኤቷል ወሳኝ ተጫዋቹ ሃምዛ ላማር በክለቡ የሚያቆየውን የውል ጊዜ ያደሰ ሲሆን በጨዋታውን ተፅእኖ ይፈጥራሉ ተብሎ የሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡ የ2010 ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊ ፉስ ራባት ሶስ ላይ አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚወስደውን መንገድ ለማሳመር ወደ ሜዳ ሲገባ ኤቷል ከሽንፈት ለመመለስ ይፋለማል፡፡

 

የማክሰኞ ውጤቶች፡

ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) 0-1 ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)

አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) 1-2 ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ)

 

ረቡዕ ሰኔ 22/2008

15፡00 – ሚዲአማ (ጋና) ከ ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ)(ኤሲፖንግ ስፖርት ስታዲየም)

22፡00 ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) ከ ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ) (ስታደ ኦሎምፒክ ደ ሶስ)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *