” ሽልማቱን ጠብቄው ነበር” – የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች አስቻለው ታመነ

የኢትየጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትላንት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ የውድድር ዘመኑ ኮከብ ተጫዋችነት ክብርም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ አምርቷል፡፡

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ደደቢትን ለቆ ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ወጣቱ የመሃል ተከላካይ ከሶከር ኢትዮጵያ ባደረገው ቆይታ በሽልማቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡

” የአመቱ ኮከብ ተብዬ በመመረጤ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚህ ደረጃ  ላይ በመድረሴም በጣም ተደስቻለው፡፡  ይህ ሽልማት የሚያኩራራኝ አይደለም ፤ ገና መነሻዬ በመሆኑ ከዚህ በኃላ ጠንክሬ በመስራት ለክለቤ እና ሀገሬ የሚጠበቅብኝን ለማድረግ እጥራለሁ” ብሏል፡፡

PicsArt_1467270619137

ሊጉ በአዲስ መልኩ በ1990 ከተጀመረ ወዲህ ከአንዋር ሲራጅ እና ደጉ ደበበ በመቀጠል የኮከብ ተጫዋችነት ክብርን ያገኘ ሶስተኛው ተከላካይ የሆነው አስቻለው መመረጡን ጠብቆት እንደነበር ይናገራል፡፡

” ሽልማቱን ጠብቄው ነበር ፤ በተለይ ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ አስቤው ነበር፡፡ ጠንክሬም ነበር ስሰራ የነበረው፡፡ ለክለቤም ማድረግ የሚገባኝን አድርጌያለው፡፡ ስለዚህ ኮከብነቱን ጠብቄው ነበር፡፡ ” ሲል ይገልጻል፡፡ አክሎም ሽልማቱ ለወየፊቱ ረጅም የእግርኳስ ጉዞው ተነሳሽነት እንደሚፈጥርለት ያምናል፡፡

” ሽልማቱ በጣም መነሳሳት ይፈጥርብኛል፡፡ ምክንያቱም ገና ወጣት ነኝ ፤ ረጅም አመት መጫወት ስለምችል በቀጣዮቹ አመታት ጥሩ ነገር እንድሰራ የሚያነሳሳኝ ይሆናል” ብሏል፡፡

አስቻለው የውድድር አመቱ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገር ከጀመረ በኋላ ከተለመደው የመሃል ተከላካይነቱ ይልቅ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ተሰልፎ የውድድር አመቱን ጨርሷል፡፡ አስቻለውም የተሰጠውን አዲስ ሚና በአግባቡ እንደተወጣ ይናገራል፡፡

” እግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን የሚሰጥህን የቤት ስራ ለመስራት መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡  አሰልጣኙ አምኖብኝ በዚህ ቦታ መጫወት አለብህ ካለ ሀላፊነትህን መወጣት ይኖርብሃል፡፡ በተጨማሪም በቦታው ተጫዋቾች ተጎድተውብን ስለነበር ያንን ቦታ ለመሸፈን ነበር የተጫወትኩት፡፡ ይህንንም በብቃት ሀላፊነቴን ተወጥቻለው” ሲል የሚና ለውጡ ተፅእኖ እንዳልፈጠረበት ገልጿል፡፡ በመጨረሻም የተሳካ የውድድር ዘመን እንዲያሳልፍ የረዱትን አመስግኗል፡፡

” ለዚህ ክብር እንድበቃ ለረዱኝ የክለቤ ተጨዋቾች ፣ ደጋፊዎች እንዲሁም ቤተሰቦቼን ከልብ አመሰግናለው”

PicsArt_1467270684850 PicsArt_1467270880604 PicsArt_1467270731383

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *