ኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በሀዋሳ በደማቅ ሁኔታ መካሄዱን ቀጥሏል፡፡ ዛሬ በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካቾች ታጅበው በተካሄዱ ጨዋታዎችም ወደ ፍፃሜው የተሸጋገሩ ቡድኖች ታውቀዋል፡፡
07:30 ላይ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ደደቢት ዳሽንን ገጥሞ 3-0 በማሸነፍ ለፍፃሜው መብቃቱን አረጋግጧል፡፡
ሰናይት ባሩዳ የግል ብቃቷን ተጠቅማ ሁለት ግሩም ጎሎች ከመረብ ስታሳርፍ ከዕረፍት መልስ ተቀይራ የገባችው ቤዛ ታደሰ የደደቢትን የማሰረጊያ ጎል አስቆጥራለች፡፡ በዕለቱ ጨዋታ ምርጥ ብቃቷን ያሳየችው የደደቢቷ ግብ ጠባቂ ሊያ ሽብሩ በርካታ ጎል የሚሆኑ ኳሶችን ከማዳኗ ባሻገር ፍፁም ቅጣት ምትም በማዳን ለቡድኗ ድል ከፍተኛውን ሚና ተጫውታለች፡፡
በሙሉ የውድድር ዘመኑ ወጥ አቋም ያሳዩት ደደቢቶች የአምናውን የግማሽ ፍፃሜ ሽንፈት በመበቀል ወደ ፍፃሜው ተሸጋግረዋል፡፡
09:30 ላይ ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ መከላክያን ገጥሞ 5-0 በማሸነፍ ለፍፃሜ ዋንጫ በቅቷል፡፡ ሽታዬ ሲሳይ 3 ግቦቸች በማስቆጠር ሀት-ትሪክ ሰርታ ደምቃ የዋለች ሲሆን ረሂማ ዘርጋ ቀሪዎቹን ሁለት ግቦች አስቆጥራለች፡፡
በጨዋታው የንግድ ባንኳ አማካይ ቅድስት ቦጋለ ድንቅ አቋም አሳይታለች፡፡
ውድድሩ በመጪው ቅዳሜ ፍፃሜውን ሲያገኝ 04:00 ላይ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ የደረጃ ጨዋታ በዳሽን ቢራ እና መከላከያ መካከል ይደረጋል፡፡
09:00 በሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ሁለቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ሃያላን ደደቢት እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፋለማሉ፡፡
ደደቢት የውድድር ዘመኑን በድንቅ አቋም ሲያሳልፍ ካለፉት አመታት በተቀዛቀዘ አቋም የዞኑን ውድድር የጨረሰው ንግድ ባንክ በማጠቃለያ ውድድሩ ወደ ቀድሞው አቋሙ መመለሱን አሳይቷል፡፡
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የደደቢቷ ሎዛ አበራ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ሽታዬ ሲሳይ በእኩል 8 ግቦች ይመራሉ፡፡ የፍፃሜው ጨዋታም ማን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ያጠናቅቃል የሚለውን የሚለይ ይሆናል፡፡
የደደቢት እና ንግድ ባንክ አልጣኞች እና ተጨዋቾችን አስተያየት ነገ ምሽት ይዘን እንቀርባለን