ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ – የደደቢት እና ንግድ ባንክ አሰልጣኞች ስለ ነገው የፍፃሜ ጨዋታ ይናገራሉ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ነገ በሀዋሳ ከተማ ስታድየም ይጠናቀቃል፡፡ በሴቶች እግርኳስ የአመቱ ታላቅ ጨዋታ በደደቢት እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል ይደረጋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በዞን ውድድር አንደኛ እና በመሆን አጠናቀው ወደ ሀዋሳ ያመሩ ሲሆን በማጠቃለያው ውድድርም ተጋጣሚዎቻቸውን በሙሉ አሸንፈው ለፍፃሜው ደርሰዋል፡፡

የደደቢቱ አሰልጣኝ ፍሬው ሃ/ማርያም የነገው ጨዋታ የውድድር ዘመኑ ግባቸውን የሚያሳኩበት እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

” ደደቢት በዚህ አመት ሰንቆ የተነሳው ሁለት ነገር ነው፡፡ ይህም የዞኑ እና የማጠቃለያው ውድድር ዋንጫን ማንሳት፡፡ የመጀመርያውን አሳክተናል ፤ ሁለተኛውን ዋንጫ ለማሳካት ነው እዚህ የተገኘነው፡፡ ”

” በርግጠኝነት ዋንጫ እንወስዳለን፡፡ ምክንያቱም የተጫዋቾቼ ተነሳሽነት ፣ ፍላጎት ፣ በራስ መተማመን እና የቡድን መንፈስ መልካም በመሆኑ እቅዳችንን እናሳካለን” ብለዋል፡፡

PicsArt_1467396747638

ከንግድ ባንክ ጋር ለ4ኛ ተከታታይ አመት ቻምፒዮን ለመሆን የተቃረቡት አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በበኩላቸው የዋንጫ ሪኮርዳቸው ቡድናቸውን ለቻምፒዮንነት እንደሚያነሳሳ ያምናሉ፡፡

” በዞኑ ውድድር ደደቢት በስምንት ነጥብ ሲርቀን ትኩረታችንን ወደማጠቃለያው በማድረግ ጉልበት የመሰሰብሰብ ስራ ሰርተን አሁን ላለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡

” ለዋንጫ ጨዋታ እኔም ሆንኩ ንግድ ባንክ አዲስ አይደለንም፡፡ ይህንን የስኬት ታሪክ በመጠቀም ተጫዋቾቼ ላይ ጠንካራ ስነ ልቦና በመገንባት ይህን ዋንጫ እንደማሳካው ሙሉ ተስፋ አለኝ ” ሲሉ አሰልጣኝ ብርሃኑ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ንግድ ባንክ ዘንድሮ በአንፃራዊነት ደከም ያለ የውድድር ዘመን ቢያሳልፍም በማጠቃለያ ውድድሩ ወደ ቀድሞ አስፈሪነቱ ተመልሷል፡፡ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም የውድድር ዘመኑን ሁለት መልኮች ያብራራሉ፡፡

” የመካከለኛ-ሰሜን ዞን ዋንጫን ለደደቢት አሳልፈን ሰጥተናል፡፡ ይህም የሆነበት አንዳንድ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ አንደኛ ደደቢትን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ላይ ካሸነፍን በኃላ ተዘናግተን ነበር፡፡ ሁለተኛው የአልጄሪያው ጨዋታ ነው፡፡ ለሀገርህ ትደክማለህ ፤ አንዳንዴ ይሳካልሀል ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አይሳካልህም፡፡ በዚህ ሁኔታ ከተመልካቹ ይሰነዘር የነበረው ከስፖርታዊ ጨዋታ ውጪ የነበሩ  ቃላት የተጫዋቾቹን ስሜት የሚጎዳ ነበር፡፡ ይሄ ይሄ ተደማምሮ በልጆቼ ላይ ትልቅ የስነ ልቦና ጫና ፈጠሯል፡፡ እኔም በተቻለኝ አቅም ልጆቼን የማረጋጋት የበረታታ ስራ ስሰራ ነበር፡፡ ” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አሰልጣኝ ፍሬው ስለ ብርሃኑ

” አሰልጣኝ ብርሃኑ ካወቅኩት ጊዜ ጀምሮ ለሴቶች እግር ኳስ የሚደክምና የሚለፋ ሰው ነው፡፡ ለሀገር ጥሩ አስተዋፅኦ ያደረገ አሰልጣኝ ነው፡፡ ከሰዎች የምትማረው ሁሉ ነገራቸውን ነው፡፡ እርሱ ደግሞ የሴቶች እግር ኳስ ሞዴል ነው፡፡ ስለዚህ ከሱ ብዙ እማራለው ብዬ ስለማስብ ሀሳቦችን ሼር እያደረግን እንሄዳለን ብዬ አስባለው ”

አሰልጣኝ ብርሃኑ ስለ ፍሬው

” ፍሬው ወጣት አሰልጣኝ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ስኬት አስመዝግቧል፡፡ ስለ ሴቶች እግርኳስ ለማወቅ እና ለመማርና ከእኛ ለመረዳት ያለው ፍላጎት በጣም ደስ ይለኛል፡፡ በጣም ጠንካራና ለወደፊቱ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ብዬ የማስበው አሰልጣኝ ነው “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *