ሎዛ አበራ እና ሽታዬ ሲሳይ ለከፍተኛ ግብ አግቢነት ተፋጠዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ነገ በደደቢት እና ንግድ ባንክ መካከል በሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ይገባደዳል፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ትልቁን ስፍራ ከሚይዙት ሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ ጎን ለጎን የቡድኖቹ ፊት አውራሪዎች ሎዛ አበራ እና ሽታዬ ሲሳይ ፉክክርም ይጠበቃል፡፡

ሁለቱም አጥቂዎች በማጠቃለያው ውድድር  8 ግቦች ከመረብ በማሳረፍ ለከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብር የተፋጠጡ ሲሆን የነገው ጨዋታ ማን ክብሩን እንደሚወስድ መልስ የሚሰጥ ሆኗል፡፡

በዞኑ ውድድር 47 ግቦች ከመረብ በማሳረፍ አንፀባራቂ የውድድር ዘመን ያሳለፈችው ሎዛ አበራ ከደደቢት ጋር የመጀመርያዋን የሊግ ዋንጫ ለማንሳት እንደተዘጋጀች ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግራለች፡፡

” ፈጣሪ ይመስገን ለዚህ ደርሰናል፡፡ እንደ ቡድን በመጫወታችንና የቡድን ህብረታችን ጥሩ በመሆኑ ለፍፃሜው ጨዋታ ደርሰናል፡፡ ለዚህም ጨዋታ የሚከፈለውን መሰዋትነት በመክፈል ክለባችንን ውጤታማ እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ” ብላለች፡፡ አክላም የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ክብር ዳግም ስለመውሰድ ተናግራለች፡፡

“ነገ ለቡድን ድል እና ለግሌም ክብር ነው የምጫወተው፡፡ በጨዋታው ብዙ ፈተና ሊገጥመን ይችላል፡፡ እነዚህን ፈተናዎች በመቋቋምና የምችለውን ሁሉ በማድረግ ለክለቤም ለራሴም ጥሩ ነገር ሰርቼ ሁለቱንም እንደማሳካ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ”

በዞን ውድድሩ ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ ግብ ማስቆጠር ያልቻለችው ሽታዬ ሲሳይ በማጠቃለያው ውድድር ተነቃቅታለች፡፡ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው ቆይታም በተደጋጋሚ ያነሳችውን የሊግ ዋንጫ ለማንሳት ያላትን ተነሳሽነት ገልፃለች፡፡ አምና ያጣችውን የኮከብ ግብ አግቢነት ክብር ዘንድሮ ለማግኘት እንዳለመችም ተናግራለች፡፡
” በተደጋጋሚ ዋንጫውን ማንሳታችን ለዋንጫ ያለንን ረሃብ አይቀንሰውም፡፡ በግሌ ድል ማድረግ በጣም ነው የምወደው፡፡ ሁሌም ለዋንጫ ስንቀርብ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ጨዋታ ወደ ሜዳ ስገባ አዲስ ነው የምሆነው፡፡ ያ ያለፈኩበት ታሪክ አያዘናጋኝም ፤ የዋንጫ ጨዋታ ሲሆን ደግሞ በጣም ነው የምራበው፡፡

” ይህን ድል በጣም ነው የምንፈልገው፡፡ የማጠቃለያ ውድድር መኖሩ በጣም ጥሩ ነው፡፡ የዞን ውድድር ብቻ ቢሆን በነጥብ ስለሆነ በጣም ነበር የምንቆጨው፡፡ ዋንጫውን ላናገኘው እንችል ነበር፡፡ ይህ ውድድር በመኖሩ እንደአዲስ ተነሳሽነት ፈጠሮብን ለፍፃሜ ደርሰናል፡፡

የቡድናችንን ተነሳሽነት ለተመለከተ ዋንጫ አንስተን የማናውቅ ነው የሚመስለው፡፡ እንደ ፈጣሪ ፍቃድ እናሳካዋለን ብዬ አስባለው፡፡

” ብዙ ጊዜ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኜ አጠናቅቄያለሁ፡፡ የኔን ያህል ኮከብ  ሆኖ የጨረሰ የለም፡፡ አምና ያጣሁትን ክብር ለማካካስ ነው የምመኘው፡፡ አምና በዚህ ቶርናመት ነበር ያጣሁት ፤ ይህች ቀን እስክትመጣም በጉጉት ነበር ስጠብቃት የነበረው፡፡ እንደማሳካው ደግሞ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ”

PicsArt_1467304193389

ሽታዬ ስለ ሎዛ

” ሎዛ በጣም የማደቃት ፣ የማከብራት ጎበዝ ተጨዋች ናት፡፡ በጭር ጊዜ ውስጥ በዚህ ደረጃ በመገኘቷ ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ምክንያቱም የእሷ እኩዮች እንደሷ አልሆኑም፡፡ ከዚህ ቀደም እኛን የሚተካ የለም ይባል ነበር፡፡ አሁን ሎዛ በሚገባ እኛን ተክታለች፡፡ እሷንም እያዩ ብዙ ተተኪዎች ይመጣሉ፡፡ ፈጣሪ ጉልበቷን ይባርክላት፡፡ ”

PicsArt_1467401506328

ሎዛ ስለ ሽታዬ

” እወነት ለመናገር ሽታዬ በጣም የማደንቃት አጥቂ ናት፡፡ የውሸት ወይም የሽንገላ አይደለም፡፡ በጣም የማደንቃት ትልቅ አጥቂ ናት፡፡  በክለብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ለሀገሯ ብዙ መሰዋትነት የከፈለች አጥቂ ናት፡፡ በዛ ላይ እሷ ላይ ደርሼ ከእርሷ ጋር በመፎካከሬ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ማለትም ከሷ በኃላ ነው የመጣሁት እሷ ላይ ደርሼ መፎካከርና በብሄራዊ ቡድን አብሬያት መጫወቴ ያስደስተኛል፡፡ ከእርሷ የምማረው ብዙ ነገር አለ፡፡ ለሽታዬ ትልቅ አክብሮት አለ፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *