ሊግ ዋንጫ ፡ የአዳነ ግርማ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ግማሽ ፍፃሜው አሸጋግሮታል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ (ሊግ ዋንጫ) ሩብ ፍፃሜ  ዛሬ አዳማ ላይ አንድ ጨዋታ ተካሂዶ ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከተማን 3-2 በመርታት ወደ ግማሽ ፍጻሜ ተሸጋግሯል፡፡

የሊጉ ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ ከባድ ፈተና ቢገጥመውም የማታ ማታ ድል አድርጎ ወጥቷል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ የእንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው አርባምንጮች አማኑኤል ጎበና ከግብ ክልላቸው ርቀው ሲከላከሉ የነበሩትን የጊዮርጊስ ተከላካዮች አምልጦ ባስቆጠረው ግብ ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡
PicsArt_1467479841763

ጉሽሚያዎች ፣ እሰጥ እገባዎች እና ድንቅ የጨዋታ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ዘግይተው ወደ ጨዋታው ሪትም መግባት የቻሉት ጊዮርጊሶች በሳላዲን ሰኢድ ግብ አቻ ሲሆኑ አርባምንጭ ከተማ በተሾመ ታደሰ ግብ በድጋሚ ወደ መሪነት ተመልሷል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኀላ ማፈግፈግ የመረጡት አርባምንጮች የኀላ ኀላ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ አዳነ ግርማ በ83ኛው እና ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃ ሲቀረው አከታትሎ ከመረብ  ያሳረፋቸው ግቦች በመጨረሻም ፈረሰኞቹን ወደ ግማሽ ፍጻሜው አሳልፏቸዋል፡፡

የጥሎ ማለፉ ግማሽ ፍጻሜ በመጪው ማክሰኞ ሲካሄድ አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ08:00 ይጫወታሉ፡፡ 10:00 ላይ ደግሞ የአምናው ቻምፒዮን መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፋለማሉ፡፡

የአዲስ አበባ ስታድየም ሜዳ በመጨቅየቱ የዛሬውን ጨዋታ ጨምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ የሚካሄዱት ጨዋታዎች በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ይደረጋሉ፡፡

Leave a Reply