የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ትላንት ፍፃሜውን ሲያገኝ ደደቢት ሎዛ አበራ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች ታግዞ ንግድ ባንክን 2-0 በመርታት ቸምፒዮን ሆኗል፡፡
እጅግ የተሳካ የውድድር ዘመን ያሳለፈችው ሎዛ በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ማጠቃለያ በ6 ጨዋታ 10 ግቦችን አስቆጥራ ለሁለተኛ ተከታታይ አመት የኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ክብር ስትቀዳጅ በአጠቃላይ በሊጉ 57 ግቦችን በማስቆጠር ሪኮርድ ጨብጣለች፡፡
ሎዛ አበራ ከፍፃሜው ጨዋታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠችውን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
ስለ ውድድሩ
በሀዋሳ በጣም አሪፍ ቆይታ ነበረን፡፡ በ15 ቀን ውስጥ ሁሉም ያላቸውን አቅም ያሳዩበት ነበር፡፡ እኛም እንደ ቡድን በህብረት በመጫወታችን አሸናፊ ሆነናል፡፡ ለዚህም ፈጣሪዬን አመሰግናለው፡፡
ኮከብ ጎል አስቆጣሪ መሆኗ የፈጠረባት ስሜት
በመጀመርያ የቡድን አጋሮቼን ማመስገን እፈልጋለው፡፡ እግር ኳስ የአንድ ሰው ስራ ስላልሆነ ሁሉም ለኔ መሰዋትነት ከፍለዋል፡፡ በተለይ ዛሬ ለኔ ነበር መስዋትነት ሲከፍሉ የነበሩት ፤ ለዚህም ደጋግሜ የቡድን አጋሮቼን ማመስገን እፈልጋለው፡፡ በግሌ በጣም ከፍተኛ የደስታ ሰሜት ተሰምቶኛል ፤ ቡድኔም ቻምፒዮን በመሆኑ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡
የጎል አነፍናፊነት ብቃት
ያው አጥቂ እንደመሆኔ መጠን ከኔ የሚጠበቅብኝን ስራ ለመስራት ሁሌም በጣም ዝግጁ ነኝ፡፡ የምችለውን ነገር ሁሉ አደርጋለው ፤ ብዙ ስህተቶች ሊኖሩብኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁሌም ከኔ የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ጠንክሬ በመስራቴ ይሆናል ስኬታማ የሆንኩት፡፡
ቀጣይነት
ያው ገና ብዙ አልሰራሁም ብዬ አስባለው፡፡ በቅርቡ ነው በትልቅ ደረጃ መጫወት የጀመርኩት ፤ ብዙ ነገር ማድረግ ይቀረኛል፡፡ ራሴን ጠብቄ ለሀገሬ ብዙ መስራት እፈልጋለው፡፡ ከሀገር ውጪ በመጫወት እራሴን ማሳየት እፈልጋለው፡፡ እነዚህን ለማድረግ አላማ ስላለኝ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፡፡ ለዚህም ፈጣሪ ይረዳኛል፡፡
በመጨረሻም. . .
ይህን ቀን በጣም እጠብቀው ነበር፡፡ ክለቤ አሸናፊ በመሆኑ እኔ ደግሞ በኮከብ ግብ አግቢነት በማጠናቀቄ ደስ ብሎኛል፡፡ በጣም የተሳካ አመት አሳልፌያለሁ፡፡ ለዚህ ለረዱኝ ሁሉ ምስጋና አቀርባለው፡፡