ሽመልስ በቀለ በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ 2 ግቦች አስቆጥሯል

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 34ኛ ሳምንት ጨዋታ ፔትሮጀት ሊጉን በድል ያጠናቀቀበትን ድል ኢቲሃድ ኤል ሾርታ ላይ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ 70 ደቂቃዎችን መሰለፍ የቻለው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ሽመልስ በቀለም ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከሊጉ ቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው ኤል ሾርታ ከሜዳው ውጪ ስዌዝ ላይ በአል ስዌዝ ስታዲየም በፔትሮጀት 3-0 ተሸንፎ መጥፎ የውድድር ዓመቱን አጠናቅቋል፡፡ ፔትሮጀት ከፍተኛ ግብ አግቢውን አህመድ ጋፍር ሳይዝ ወደ ጨዋታው የገባ የአጥቂ መስመሩን ሽመልስ በቀለ በሚገባ መሸፈን ችሏል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በ19ኛው ደቂቃ ፔትሮጀት በሽመልስ ግብ ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡ በ37ኛው ደቂቃ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመዘዘበት ሽመልስ በ61ኛው ደቂቃ መሪነቱን ወደ ሁለት ማስፋት ችሏል፡፡ ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ በናይጄሪያዊው ጄምስ ኦዎቦስኪኒ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ የማሳረጊያውን ግብ በተጨማሪ ደቂቃ ከመሰብ ያሳረፈው ሙስጠፋ ሺያታ ነው፡፡

በ2015/16 የግብፅ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን የአጥቂ አማካዩ ሽመልስ አንድ ሐት-ትሪክ ጨምሮ 6 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

የኡመድ ኡኩሪው ኢኤንፒፒአይ በመሃመድ ኤል ሻሚ እና መሃመድ አህመድ ካምል ግቦች ምስር ኤል ማቃሳን 2-0 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን አጠናቅቋል፡፡

በደረጃ ሰንጠረዡ ፔትሮጀት በ46 ነጥብ 11ኛ እንዲሁም ኢኤንፒፒአይ በ47 ነጥብ 10ኛ በመሆን ሊጉን አጠናቅቀዋል፡፡ ሊጉን አንድ ጨዋታ የሚቀረው ሻምፒዮኑ አል አሃሊ በ75 ነጥብ ሲመራ በተመሳሳይ አንድ ጨዋታ የሚቀረው እና የውድድር ዓመቱን አሰልጣኝ በማሰናበት የተጠመደው ዛማሌክ በ68 ነጥቦች ሁለተኛ ሆኖ መጨረሱን አረጋግጧል፡፡

አራት ቀሪ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች የሚቀሩ ሲሆን ቻምፒዮኑ እና ወራጆቹ በመታወቃቸው ዋናኛ ፋክክሩ ሶስተኛ ሆኖ የካፍ ካንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳታፊነትን ለማግኘት በአል መስሪ እና ሰሞሃ መካከል ይሆናል፡፡ ሁለት ነጥብ ብቻ የሚለያያቸው ሁለቱ ክለቦች ሶስተኛ ሆኖ ሊጉን ለማጠናቀቅ ይፋለማሉ፡፡ የሊግ ክብሩን ለባላንጣው አል አሃሊ አሳልፎ የሰጠው ዛማሌክ በጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ቀያዮቹን ሰይጣኖች በካይሮ ደርቢ የሚያስተናግድበት ታላቁ የአፍሪካ ደርቢም ከወዲሁ ይጠበቃል፡፡

የሽመልስ በቀለን ግብ ለመመልከት ይህንን ሊንክ ይጫኑ :- You Tube

Leave a Reply