ደጉ ደበበ ራሱን ከብሄራዊ ቡድን ማግለሉን በሰርጉ እለት ይፋ አደረገ

ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ራሱን ከብሄራዊ ቡድን እንዳገለለ ሲነገርና ሲስተባበል የሰነበተው የደጉ ደበበ ጉዳይ መቋጫ አግኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል ደጉ ደበበ ባለፈው ቅዳሜ ባከበረው የሰርግ ስነስርአት ላይ ራሱን ከብሄራዊ ቡድን እንዳገለለ በይፋ ማስታወቁን ልሳነ ጊዮርጊስ ዘግቧል፡፡

ከ1995 ጀምሮ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 50 የሚጠጉ ጨዋታዎችን ያደረገው ተከላካይ ስለ ውሳኔው ሲያስረዳ ‹‹ ከ10 አታት በላይ ለሀገሬ ያለኝን አበርክቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ሙሉ ትኩረቴን ለክለቤ እና ለቤተሰቤ መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ራሴን ለማግለል ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ ›› ብሏል፡፡

ደጉ ደበበ በብሄራዊ ቡድን ባሳለፈው ጊዜ እንደሚኮራ ይናገራል፡፡

‹‹ ሁሉንም ነገር ወደ ኃላ መለስ ብዬ ሳስበው ኩራት ይሰማኛል፡፡ ወደፊት ለልጆቼ የምነግራቸው ብዙ መልካም ነገር እንደሰራሁ ይሰማኛል፡፡ በየመንገዱ እና በተያዩ ቦታዎች ህዝቡ የሚሰጠኝ አክብሮት የበለጠ እንድጫወት ቢያነሳሳኝም ክለቤን በሚገባ ለማገልገል ካለኝ ፍላጎት በመነሳት ራሴን አግልያለሁ፡፡

‹‹ መላው የኢትዮጵያ ህዝብን ፣ በተለያዩ ጊዜያት አብረውኝ የተጫወቱ ተጫዋቾች ፣ የአርባምንጭ ህዝብን ፣ ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞች በሙሉ እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እና ሰራተኞች በሙሉ ማመስገን ይገባኛል፡፡ ቀሪውን ጊዜዬንም ለዚህ ክብር ላበቃኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለኝን ጥልቅ ክብር ያለኝን ነገር ሁሉ መስጠቴን እቀጥላለሁ፡፡ ›› ሲል ሃሳቡን ደምድሟል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ