የ2008 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ (ሊግ ዋንጫ) ነገ ይፈፀማል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአምናው የጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን መከላከያ የሚያደርጉትን ጨዋታ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
መከላከያ በቅርብ አመታት ለዚህ ውድድር የተሰራ እስኪመስል ድረስ ድንቅ አቋም እያሳየ ይገኛል፡፡ ዘንድሮው በ4 አመት ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ወደ ፍጻሜው ያለፈ ሲሆን በሁለቱ ፍጻሜዎች ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ ዋንጫ አንስቷል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከሌሎች ተጋጣሚዎች በተለየ መልኩ ጥሩ አቋም ከማሳየታቸው በተጨማሪ ወደ ፍፃሜ ያለፉት ንግድ ባንክን በቀላሉ አሸንፈው ነው፡፡ የክለቡ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ግን የጥሎ ማለፍ ስፔሸሊስት መሆናቸውን ለማሳየት የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ እንደሚገባቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ይህን ለማለት የነገውን ጨዋታ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ የአፍሪካ ውድድር ተሳትፏችንን አረጋግጠናል ፤ ነገር ግን ዋንጫውን በማንሳት ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ገብረመድህን ስለነገው ጨዋታ ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰጡት አስተያየትም ፈረሰኞቹ በቅርቡ የሊጉ ቻምፒዮን በመሆናቸው በጠንካራ ራስ መተማመን ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ በእለቱ የተሻለው ቡድን ያሸንፋል፡፡ በእኛ በኩል ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ እነሱ የሊጉ ቻምፒዮን በመሆናቸው በራስ የመተማመን መንፈሳቸው ጠንካራ ነው፡፡ ነገር ግን እኛም ከነሱ አንሰን የምንገባበት ምክንያት የለም፡፡
‹‹ጨዋታው የፍጸሜ እንደመሆኑ መሸናነፍ ግዴታ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስንገናኝ እነሱም ያሸንፉናል ፣ እኛም እናሸንፋቸዋለን፡፡ ስለዚህ ነገ እነሱ ለማሸነፍ እንደሚጫወቱት እኛም ድል አድርገን ዋንጫ ለማንሳት ነው የምንጫወተው፡፡ ››
የመከላከያ የማጥቃት መሳርያ የሆነው ፍሬው ሰለሞን በክለቡ ስኬት ደስተኛ መሆኑን በመግለጽ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንደተዘጋጁ ተናግሯል፡፡
‹‹ በ4 አመት ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ በፍፃሜው ላይ መገኘታችን እና ለካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከወዲሁ ማለፋችንን በማረጋገጠጣችን ክብር ይሰማኛል፡፡ የነገውንም ጨዋታ አሸንፈን ቻምፒዮን ለመሆን የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን›› ብሏል፡፡
ከሳምንት በፊት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ በጥሎ ማለፉ ሁለት ጨዋታዎች ከአርባምንጭ እና አዳማ ከተማ ፈተና ቢገጥመውም ፍጻሜውን ከመቀላቀል ያገደው ነገር የለም፡፡ በነገው እለትም ከ2001 በኋላ የሁለትዮሽ ድል ለማስመዝገብ በማለም ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ የክለቡ ረዳት አስልጣኝ ፋሲል ተካልኝም ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንጊዜም ክብርን እንደሚያስቀድም ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
‹‹አንዳንድ ጊዜ ክብር ከሁሉም ነገር ይበልጣል፡፡ በእያንዳንዱ ውድድር ላይ ስንሳተፍ ራሳችንን ለማስከበር ነው የምንጫወተው፡፡ ነገም ወደ ሜዳ የምንገባው ዋንጫውን ለማንሳት ነው፡፡ ከትላንቱ ጨዋታ አንዳንድ ስህተቶቻችንን አርመን የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍና የምንችለውን ሁሉ ለመስጠት ተዘጋጅተናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡
በሩብ ፍጻሜው አርባምንጭ ከተማን ሁለት ጊዜ ከመመራት አንሰራርተው እንዲያሸንፉ የረዳውና አዳማ ከተማን በመለያ ምት ሲረቱ የማሸነፍያ ገሉን ያስቆጠረው አዳነ ግርማም የፋሲል ተካልኝን ሀሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ‹‹ ጨዋታው የክብር ነው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ሁልጊዜም የአሸናፊነት መንፈስ አለ፡፡ በአመቱ መጀመርያ ላይ ስናቅድ ሁለቱንም ዋንጫ አስበን በመሆኑ ጨዋታውን አሸንፈን የውድደረር ዘመኑን በሁለትዮሽ ድል መደምደም እንፈልጋለን፡፡ ›› ብሏል፡፡
አዳነ ግርማ ከጨዋታው ጎን ለጎን የጸጥታ ስጋት እና የደጋፊዎች ስርአት አልበኝነት አሳሳቢ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ‹‹ ውድድሩ በጣም ቀዝቃዛ ነው፡፡ ደጋፊው እንደልቡ በነፃነት ድጋፉን ሲሰጥ ነው ደስ የሚለው፡፡ በትላንትናው ጨዋታ ካለ ደጋፊዎቻችን ተጫውተናል፡፡ ለእኛ ያለ ደጋፊ መጫወት ከባድ ነው፡፡ ክለባችንም ሆነ የሌሎች ደጋፊዎች ማህበራት ፣ ፌዴሬሽኑ እና የሚመለከታቸው አካላት ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት ስራ ሊሰሩ ይገባል›› ብሏል፡፡
እንዴት መጡ?
መከላከያ በመጀመርያው ዙር ወላይታ ድቻን በቀላሉ 3-0 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ ሲሸጋገር በሩብ ፍፃሜው ደደቢትን በባዬ ገዛኸኝ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ 1-0 አሸንፎ ግማሽ ግፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡ ትላንት ደግሞ ንግድ ባንክን በግማሽ ፍፃሜው ገጥሞ 3-0 በማሸነፍ ለፍፃሜው መብቃት ችሏል፡፡
መከላከያ በዘንድሮው ሊግ ዋንጫ
ተጫወተ – 3
አስቆጠረ – 7
ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ – ባዬ ገዛኸኝ (3)
ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፈው የውድድር ዘመን ፕሪሚየር ሊግን በቻምፒዮንነት በማጠናቀቁ በቀጥታ ወደ ሩብ ፍፃሜ ሲያልፍ ቅዳሜ እለት አርባምንጭ ከተማን ሁለት ጊዜ ከኋላ ተነስቶ በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ተሸጋግሯል፡፡ ትላንት ከአዳማ ከተማ ጋር በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 ተለያይቶ በተሰጠው የመለያ ምት ወደ ፍፀሜ አልፏል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው ሊግ ዋንጫ
ተጫወተ – 2
አስቆጠረ – 4
ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ – ሳላዲን ሰኢድ እና አዳነ ግርማ (2)
የታሪክ ጦርነት
በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ እንደ ሁለቱ ክለቦች በዋንጫዎች ያሸበረቁ ክለቦች የሉም፡፡ የቀድሞው ኃያል ክለብ መከላከያ ከረጅም ጊዜያት መጥፋት በኋላ በቅርብ አመታት ዋንጫዎችን ማንሳት የጀመረ ሲሆን ጥሎ ማለፉን ለ13 ጊዜ በማንሳት ባለ ሪኮርድ ክለብ ነው፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን ከሳምንት በፊት ያነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ፕሪሚየር ሊጉ በጥሎ ማለፉ የቅርብ አመታት ታሪክ በርካታ ዋንጫዎችን ባያነሳም ከአዲሱ ሚሌንየም ወዲህ በተደረጉ ውድድሮች ዋንጫዎችን ለማንሳት ተቃርቦ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአጠቃላይ 10 ዋንጫዎችን በማንሳት ከመከላከያ ቀጥሎ በጥሎ ማለፉ ስኬታማ ክለብ ነው፡፡
የቅርብ ጊዜያት ግንኙነት
ሁለቱ ክለቦች 2008 ከገባ ወዲህ 6 ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡ ከ2007 ወደ 2008 በተሸጋገረው የጥሎ ማለፍ ግማሽ ፍፃሜ መከላከያ 2-1 ሲያሸንፍ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመለያ ምቶች አሸናፊ ሆኗል፡፡ በአአ ከተማ አምበር ዋንጫ የምድብ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 ሲረታ በዚሁ ውድድር ለደረጃ ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸንፏል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመርያ ዙር ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ሲያሸንፍ በሁለተኛው ዙር 1-1 አቻ ተለያይተዋል፡፡
የጉዳት እና ቅጣት ዜናዎች
በቅዱስ ጊዮርጊስ ሮበርት ኦዶንካራ በጉዳት የማይሰለፍ ሲሆን ምንያህል ተሾመ የሚገኘው ካናዳ በመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡
ተስፋዬ አለባቸው ከ5 ጨዋታ ቅጣት ሲመለስ ራምኬል ሎክ ከመጠነኛ ጉዳቱ አገግሞ ለነገ ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል፡፡
በመከላከያ በኩል አስቀድመው የረጅም ጊዜ ጉዳት ያለባቸው ሙሉአለም ጥላሁን ፣ ነጂብ ሳኒ እና ምንይሉ ወንድሙ የማይኖሩ ሲሆን የጥሎ ማለፉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ባዬ ገዛኸኝ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡