በኢትዮጵያ ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡና ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ

የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) ዛሬ አንድ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም አስተናግዶ ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ቀጣዩ ዙር አሳልፏል፡፡ 11 ሰአት ላይ በተደረገው የዳሸን ቢራ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ አደገኞቹ 2-0 አሸንፈው የቅዳሜውን ድል ደግመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ግብ ያስቆጠረው ገና ጨዋታው በተጀመረ በ9ኛው ደቂቃ ላይ በኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ነው፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ ይበልጥ የተነቃቁት ቡናዎች በአስቻለው ግርማ ፣ ቢንያም አሰፋ እና ኤፍሬም አሻሞ ግብ የማግባት እድሎችን ቢፈጥሩም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡ በተለይም አስቻለው ግርማ ከግብ ጠባቂው ጋር በአንድ ለአንድ አጋጣሚ ያባከናት እድል ተጠቃሽ ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ዳሸን ቢራ የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር አልፎ አልፎ ጫናዎችን መፍጠር ቢችሉም የአስቻለው ግርማ የ78ኛ ደቂቃ ግብ ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፍ መንገዱን ጠርጋለች፡፡

በጨዋታው ቢንያም ታዬ እና ዳዊት እስጢፋኖስ አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ የታዩ ሲሆን ዳኞቹም በሚገባ መናበብ ጨዋታውን መቆጣጠር ተስኗቸው ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ