ኢትዮጵያ ቡና እና ዳሸን ቢራ በ5 ቀን ውስጥ ለ2ኛ ጊዜ ይፋለማሉ

የኢትዮጵያ ዋንጫ ዘንድሮም እንዳለፉት ጥቂት አመታት በጥቂት ክለቦች ብቻ መካሄዱን ቀጥሏል፡፡ 16የሊጉ ክለቦች ብቻ ባሳተፈው የዘንድሮው ውድድር የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች በጥቅምት መጨረሻ የተካሄዱ ሲሆን ዛሬ በ11 ሰአት ኢትዮጵያ ቡና ከ ዳሸን ቢራ በሚያደርጉት ጨዋታ ይቀጥላል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ቅዳሜ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተጫውተው ኢትዮጵያ ቡና 2-1 ያሸነፈ ሲሆን ከ4 ቀናት በኃላ በሚያደርጉት ፍጥጫ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች እንደሚያሸንፉ እየተናገሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ‹‹ ዳሽን ቢራ የሊጉ አዲስ ክለብ ቢሆንም ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ አሁን በወራጅ ቀጠና ውስጥ ቢገኙም ለተጋጣሚያችን ክብር እንሰጣለን፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ባደረግነው ጨዋታ በሚገባ በመመልከታችን የዛሬውንም ጨዋ በእርግጠኝነት እናሸንፋለን ›› በማለት ለሊግ ስፖርት የተናገሩ ሲሆን በተመሳሳይም የዳሽን ቢራው አሰልጣኝ ካሊድ መሃመድም ያለፈው እንደማይደገም አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹ ኢትዮጵያ ቡና ጠንካራ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ቢሆንም የዛሬውን ጨዋታ በድል ለመወጣት ተዘጋጅተናል፡፡ ባለፈው ጨዋታ የሰራናቸው ስህተቶችን አርመን ወደ ሜዳ እንገባለን ›› ብለዋል፡፡

በዛሬው ጨዋታ አማካዩ አስራት መገርሳ ከዳሸን ቢራ በኩል በጉዳት እንደማይሰለፍ ተነግሯል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ