ከሊግ ዋንጫ ፍፃሜ በኃላ የተሰጡ አስተያየቶች

ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሎ ማለፍ (ሊግ ዋንጫ) ፍጻሜ መከላከያን በመለያ ምት 4-3 በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ ከጨዋታው በኃላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች ገብረመድህን ሃይሌ እና ማርቲነስ ኤግናተስ ‘ኖይ’ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“ያገኘናቸውን የግብ ማግባት እድሎች መጠቀም አልቻልንም” ገብረመድህን ሃይሌ

ስለፍፃሜ ጨዋታ

እንግዲህ በዛሬው ጨዋታ አጠቃላይ ቡድናችን ጥሩ ነበር፡፡ አጥቅቶ ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ የተሳካ ነበር ነገር ግን ያገኘናቸውን የግብ ማግባት እድሎች መጠቀም አልቻልንም፡፡ በጣም ጥሩ ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን ስተናል፡፡ በጥሎ ማለፉ እንደዚህ አይነት ነገሮች ያጋጥማሉ፡፡ ውጫዊ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ከችግሮቹ አንፃር ሲታይ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህ ቡድን በሊግ ዋንጫ ጨዋታ ጥሩ ነው፡፡ ዛሬ እንደውም የዳኝነት ችግር ባይደርስብን አሸናፊ እንሆን ነበር፡፡ በሊግ ዋንጫው በዓመት ውስጥ የሚታዩ የዳኝነት ችግሮች ብዙ ግዜ አይታዩም ማለት ባይቻልም ግን ይቀንሳል፡፡ የአሸናፊነት መንፈሳችን ጥሩ ነው፡፡ ያው የኮንፌድሬሽን ካፕ ተሳታፊነታችን አሳክተናል ስለዚህ ጥሩ ነው፡፡

ስለቀጣዩ ጊዜ

በቀጣዩ የኮንፌድሬሽን ካፕ አዲስ የሚመጣው አሰልጣኝ ያስብበት፡፡ እኔ የመጨረሻዬ ስለሆነ ከዚህ በኃላ ነው የምሰናበተው፡፡ ውሌን ጨረሻለው፡፡ ምንም የመቀጠል ፍላጎት የለኝም፡፡ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ደግሞ በቅርቡ አለ ስለዚህ ትኩረቴን ወደእዛ አድርጋለው፡፡

“አሸናፊ የሆንነው ሳምንቱን በሙሉ ጠንካራ ልምምድ ስለምንሰራ ነው ”ማርት ኖይ

ስለጨዋታው

እኔ እንደማስበው ከሆነ ጥሩ ጨዋታ ነበር፡፡ ተጋጣሚያችን መከላከያም ጥሩ መጫወት ችሏል፡፡ በጣም ግለት እና ወጣ ውረዶች የበዙበት ግጥሚያ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ተመልካቹን እንዲዝናና አድርጓታል፡፡ አሸናፊ የሆንነው ሳምንቱን በሙሉ ጠንካራ ልምምድ ስለምንሰራ ነው፡፡ ተጫዋቾቼም ሁሌም ጠንካራ ስራን ይሰራሉ፡፡ የእኔ የስልጠና ዘዴ ከፍተኛ ጉልበትን ይጠይቃል፡፡ ትንሽ ጉሽሚያዎች የነበሩት ጨዋታ ነበር፡፡ በስምንት ቀናት ውስጥ ደረግነው አራተኛ ጨዋታችን ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በአካል ብቃቱ ረገድ ወደ ጨዋታው ለመግባት እንዲቸግረን አድርጓል፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው መመለስ ችለናል፡፡ ብዙ ዕድሎችን አምክነናል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን ማጠናቀቅ እንችል ነበር፡፡

Leave a Reply