አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ለድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝነት ከስምምነት ደርሰዋል

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ለመሆን ከስምምነት መድረሳቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከታማኝ ምንጮቿ አረጋግጣለች፡፡

የክለቡ ቦርድ ባለፈው ሳምንት አሰልጣኝ መሰረት ማኒን ከሃላፊነት ለማንሳት ከውሳኔ ላይ መድረሱን ተከትሎ ከሲዳማ ቡና ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን በአሰልጣኝነት መርጧል፡፡

አሰልጣኝ ዘላለም ከክለቡ ጋር የሁለት አመት ኮንትራት የተፈራረመው ሲሆን ክለቡ በክረምቱ ራሱን ለማጠናከርና በፍጥነት ወደ ቅድመ ዝግጅት ለመግባት እንዲረዳው በቅድሚያ የአሰልጣኝ ቅጥር ላይ ማተኮሩ ታውቋል፡፡

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በአሁኑ ወቅት የብሄራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆነው በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

የቀድሞው የሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ደደቢት እና ደቡብ ፖሊስ አሰልጣኝ ዘላለም ከአዲሱ ሚሌንየም ወዲህ ብቅ ካሉ ጥሩ አሰልጣኞች አንዱ መሆን ችለዋል፡፡

Leave a Reply