ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በዩጋንዳዊው ሃምዛ ኦሌማ ላይ ፍላጎት አሳይተዋል

ዩጋንዳዊው አማካይ ሃምዛ ኦሌማ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጫወት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።

የተጫዋቹ ወኪል ጃዬዎላ ሜሂፋ ለካዎዎ ድረገፅ እንደተናገረው ከሆነ የኢትዮጵያ እና የሃገሩ ኡጋንዳ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ተጫዋቹን ለማስፈረም በፉክክር ላይ ይገኛሉ።

“ሶስት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ኦሌማን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይተዋል። እነዚህም አዳማ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ናቸው። ዘንድሮ ወደ ዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ ያደገው ኦዱንፓራካ ክለብም የተጫዋቹ ፈላጊ ነው። ነገርግን ወደ ኢትዮጵያ ለሚደረግ ዝውውር ቅድሚያ የምንሰጥ ይሆናል፡፡ ” በማለት የድርድር ሂደቱን ገልጿል።

በመስመር አማካይ እና የክንፍ አጥቂ ስፍራዎች ላይ መጫወት የሚችለው ኦሌማ በፍጥነቱ እና ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ብቃቱ ይታወቃል። ኦሌማ ከሀገሩ ውጪ በደቡብ ሱዳኑ ክለብ አትልባራ እና በሱዳን ፕሪምየር ሊግ ለሚሳተፈው ሜሪክ ኮስቲ ክለቦች መጫወት የቻለ ሲሆን የዩጋንዳ ወጣት ብሔራዊ ቡድንም አባል ነበር።

ተጫዋቹ በሚያዝያ ወር ከቀድሞ ክለቡ ሜሪክ ኮስቲ የገንዘብ አለመስማማት እና የተሰላፊነት ዕድል ማጣትን በመጥቀስ በስምምነት ከተለያየ በኋላ ወደሃገሩ ተመልሶ በግሉ ልምምድ እየሰራ የሚገኝ በመሆኑ ወደ ቀጣይ ክለቡ በነፃ ዝውውር የሚያመራ ይሆናል።

Leave a Reply