ጋቶች ፓኖም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለውን ቀሪ የ6 ወር ውል አክብሮ በክለቡ እንደሚቆይ የተጫዋቹ ወኪል ዴቪድ በሻ ዛሬ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጧል፡፡ ተጫዋቹ ከቡና ጋር ያለው የውል ጊዜ አጭር በመሆኑ ወደ ደደቢት ሊያመራ ነው የሚሉ ወሬዎችንም ዴቪድ ሀሰት ናቸው በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
“ጋቶች ከቡና ጋር የሚያቆየው ቀሪ የ6 ወር ውል አለው፡፡ ይህንን ውልም አክብሮ ከቡና ጋር የቅድመ ዝግጅት ልምምድ ላይ ይሳተፋል፡፡ ወደ ደደቢት ሊሄድ ነው የሚሉ ወሬዎችን ስሰማ ነበር፡፡ ይህ ፈፅሞ ሃሰት ነው፡፡” ብሏል፡፡
ዴቪድ ይህን ቢልም የጋቶች የቡና ቆይታ ግን ከ6 ወር በኃላ አጠራጣሪ መሆኑን ከመግለፅ አልተገደበም፡፡ “የጋቶችን የቪድዮ ምስል በዩትዩብ ገፃችን ላይ ለቀናል፡፡ ይህንን ተከትሎ ብዙ ወኪሎች ተጫዋቹ ላይ ፍላጎታቸውን እያሳዩ ይገኛል፡፡ ከስድስት ወር በኃላ የሚፈጠረውን አላውቅም፡፡ ነገር ግን ጋቶች ከአሁን የተሻሉ ውሎች ሊመጡለት ይችላል፡፡”
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተለቀቀው ናይጄሪያዊው አጥቂ ፊሊፕ ዳውዝ ከቡና ጋር ስሙ ቢያያዝም ቀጣይ ማረፊያው ከኢትዮጵያ ውጪ እንደሆነ ዴቪድ ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ “ቡና የፊሊፕ ፈላጊ ክለብ ነበር፡፡ ወደ እኔ ወጥተው ድርድር ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ተጫዋቹ ከወዲሁ ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚገኝ ክለብ ለመጫወት ወስኗል፡፡ ውል ስላልፈረምን ከዚህ በላይ መናገር ይቸግረኛል፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ነገሮች እንደሚጠናቀቁ እምነት አለኝ” በማለት ሃሳቡን አጠናቅቋል፡፡