የውድድር ዘመኑን ላለመውረድ በመታገል የጨረሰው አርባምንጭ ከተማ በቀጣዩ አመት በጠንካራ ተፎካካሪነት ለመምጣት የወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል በማደስ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
ክለቡ በአሁኑ ሰአት የወሳኝ ተጫዋቾቹን ኮንትራት በማራዘም ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን ድንቅ የውድድር አመት ያሳለፉት ታደለ መንገሻ ፣ ተሾመ ታደሰ እና አበበ ጥላሁን በክለቡ የሚያቆያቸውን ኮንትራት ለመፈራረም በድርድር ላይ ይገኛሉ፡፡ ለውል ማደሻም ከፍተኛ ገንዘብ እያቀረበ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
ክለቡ አምበሉ አማኑኤል ጎበናን እና አበበ ጥላሁንን ለማቆየት የተቃረበ ቢሆንም የታደለ እና ተሾመ ጉዳይ እስካሁን አልባት ማግኘት አልቻለም፡፡ ሁለቱ ከፍተኛ የውል ማደሻ ገንዘብ መጠየቃቸው ሲነገር በአዲስ አበባ ክለቦች የሚፈለገው ታደለ የመቆየቱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል፡፡
ስራ አስኪያጁ አቶ ታረቀኝ ሺበሺን ከሃላፊነታቸው ያሰናበተው አርባምንጭ የመልካሙ ፉንዱሬን ፣ ወንድሜነህ በክሪ እና በረከት ወልደፃዲቅን ኮንትራት ያላራዘመ ሲሆን በውል ማደስ ዙርያ ከክለቡ ጋር መስማማት ያልቻለው ትርታዬ ደመቀ ክለቡን ሊለቅ እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ትርታዬ የእንዳለ ከበደ ወደ ክለቡ መመለስ ተከትሎ ቦታውን የተነጠቀ ሲሆን በቀኝ መስመር ተከላካይነት የውድድር ዘመኑን መጨረሱ አላስደሰተውም፡፡
አሰልጣኝ ጳውሎስ ጸጋዬ ከክለቡ ጋር እንደሚቀጥሉ ሲጠበቅ ሀብታሙ ወልዴ እና አብዮት ወንድይፍራው በውሰት ወደ ሌሎች ክለቦች ያመሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡