ኮንፌድሬሽን ካፕ፡ በሞሮኮ ደርቢ ፉስ ራባት ድል ቀንቶታል

በኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ ምድብ ሁለት ማራካሽ ላይ ከሜዳው ውጪ ካውካብ ማራካሽን የገጠመው ፉስ ራባት 3-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሁለቱም ክለቦች ከጨዋታው በፊት በኮንፌድሬሽን ካፕ የምድብ ጨዋታ ያልተሸነፉ ሲሆን የሞሮኮ ሻምፒዮኖቹም የ100% ያለመሸነፍ ሪከርድን ማስጠበቅ ችለዋል፡፡

የሱፍ ኤል ግናዊ በ23ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ፉስን ቀዳሚ ሲያደርግ ልማደናው ግብ አዳኝ መሃመድ ኤል ፋኪህ ካውካብን ክለቦቹ ወደ እረፍት ከመሄዳቸው በፊት በፍፁም ቅጣት ምት አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ አቡዱልሰላም ቤንዡለም ፉስን በ48ኛው ዳግም መሪ ማድረግ ሲችል መሃመድ ፋውዚር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ካውካቦችን ተስፋ ያስቆረጠች ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ፉስ ራባት ምድብ ሁለትን በሰባት ነጥብ መምራት ሲጀምር ካውካብ ማራካሽ በስድስት ነጥብ ይከተላል፡፡

የምድብ ጨዋታዎቹ ዛሬም ሲቀጥሉ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ያንግ አፍሪካንስ እና ሚዲአማ ዳሬ ሰላም ላይ ይጋጠማሉ፡፡ በኮንፌድሬሽን ካፑ መጥፎ አጀማመር ያሳዩት ሁለቱም ክለቦች ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ ማሸነፍን አጥብቀው ይፈልጋሉ፡፡ በሳምንቱ መጀመሪያ ያንጋ ከአንጎላው ሳግራዳ ኤስፔራንሳ ጋር ሲጫወት ተጫዋቾቹ ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ በካፍ የ10 ሺህ ዶላር ቅጣት ሲጣልበት የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ የማለፍ ተስፋውን ለማለምለም አልሟል፡፡ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ሚዲአማ በተደጋጋሚ ከውድድር ለመውጣት ቢያስብም ወደ ዳሬ ሰላም ከመጓዝ አልተገታም፡፡

የ2015 ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊው የቱኒዚያ ሻምፒዮኑ ኤቷል ደ ሳህል በሜዳው ሶስ ላይ አል አሃሊ ትሪፖሊን ያስተናግዳል፡፡ ከመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካት የቻሉት ኤቷሎች ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ ማሸነፍን አጥብቆ ይፈልጋሉ፡፡ በሊቢያ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሜዳው ያለውን ጨዋታ ገለልተኛ ሜዳ ላይ መጫወት የተገደደው የትሪፖሊው ክለብ ዝቅተኛ የማሸነፍ ግምት ተሰጥቶታል፡፡

 

የአርብ ውጤት

ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ) 1-3 ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ)

 

ቅዳሜ ሐምሌ 8 ቀን 2008

16፡00 – ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) ከ ሚዲአማ (ጋና) (ናሽናል ስታዲየም)

20፡30 – ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) ከ አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) (ስታደ ኦሎምፒክ ደ ሶስ)

Leave a Reply