ቻምፒየንስ ሊግ፡ የምድብ ሶስተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ

የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ዙር ሶስተኛ መርሃግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀምራሉ፡፡ የምድብ አንድ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ዜስኮ ዩናይትድ አሴክ ሚሞሳስን ሲያስተናግድ አል አሃሊ ዋይዳድ ካዛብላንካን ይገጥማል፡፡

ዜስኮ ዩናይትድ ሳይጠበቅ አል አሃሊን አሌክሳንደሪያ ላይ ማሸነፍ የቻለው አሴክ ሚሞሳስን በሜዳው ያስተናግዳል፡፡ ሁለቱም ክለቦች እኩል ሶስት ነጥብ ሲኖራቸው ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚስደውን መንገድ ምቹ ለማድረግ ይፋለማሉ፡፡ ዜስኮ በሜዳው ጥሩ ሪከርድ ያለው ሲሆን አሴክ በዛምቢያ ይፈተናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሁለት ጨዋታዎችን በሽንፈት የጀመረው የግብፁ ሻምፒዮን አል አሃሊ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማምራት አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ሲሆን በሜዳው በቻምፒየንስ ሊጉ ግሩም አቋም ላይ የሚገኘውን ዋይዳድ ካዛብላንካን ይገጥማል፡፡ በምድቡ አናት እና ግርጌ ላይ የሚገኙት የሁለቱ ክለቦች መሸናነፍ ምድብ ውስጥ ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን አሃሊ በቻምፒየንስ ሊጉ ለመቆየት ማሸነፍ እና ማሸነፍ ላይ ብቻ የተመሰረተ ጨዋታን ይከተላል ተብሏል፡፡

አሃሊ በዝውውር መስኮቱ ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቹን አጥቶ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ የመስመር አማካዩ ረመዳን ሶብሂ ወደ እንግሊዙ ስቶክ ሲቲ ሲያመራ የጋቦኑ ኢንተርናሽናል ማሊክ ኢቮና ከፍተኛ የገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ላይ ወደ ሚገኘው የቻይና ሊግ አምርቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አሰልጣኝ ማርቲን ዮል በጋናዊው አጥቂ ጆን አንቲው ላይ ሙሉ ዕምነታቸውን ጥለዋል፡፡

 

ቅዳሜ ሐምሌ 8/2008

15፡00 – ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) ከ አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር) (ሌቪ ሙዋናዋሳ ስታዲየም)

19፡30 – አል አሃሊ (ግብፅ) ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) (ቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም)

Leave a Reply