ኮንፌድሬሽን ካፕ፡ ያንጋ ነጥብ ሲጥል ኤቷል ድል ቀንቶታል

ብቸኛው የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ያንግ አፍሪካንስ ከሚዲአማ ጋር 1-1 ሲለያይ ኤቷል ደ ሳህል ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር አል አሃሊ ትሪፖሊን 3-0 ረምርሟል፡፡ ዳሬ ሰላም ላይ ያንግ አፍሪካንስ ከወዲሁ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ ተስፋውን ማጨለም ጀምሯል፡፡ ሚዲአማ የተሻለ እንቅስቃሴ ባደረገበት ጨዋታ ቡድኖቹ ሳይሸናነፉ 1 አቻ ወጥተዋል፡፡

ጨዋታው በተጀመረ በሶስተኛው ደቂቃ ዶናልድ ንጎማ ዶምቦ ከታንዛኒያው ኢንተርናሽናል ሳይመን ሙሱቫ የተቀበለው ኳስ ቺፕ በማድረግ ያንጋን ቀዳሚ ቢያደርግም በርናርድ ኦፎሪ ሚዲአማን አቻ አድርጓል፡፡ አባድ መሃመድ ሚዲአማ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ ሊወጣ የሚችልበትን እድል አምክኗል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ክለቦች የማለፍ ተስፋቸው እየደበዘዘ መጥቷል፡፡ ሚዲአማ በሁለት ነጥብ ሶስተኛ ሲሆን ያንጋ በአንድ ነጥብ የምድብ አንድ ግርጌን ይዟል፡፡ PicsArt_1468733544013

በዝግ ስታዲየም ሶስ ላይ አል አሃሊ ትሪፖሊን ያስተናገደው የአምናው ሻምፒዮን ኤቷል ደ ሳህል ወደ መሪዎቹ የቀረበበትን ድል አስመዝግቧል፡፡ የቱኒዚያ ሻምፒዮኖቹ በተከላካዩ አላያ ብሪጊዉ ሁለት ግቦች እና በአህመድ አኪያቺ አንድ ግብ ታግዘው አሃሊ ትሪፖሊን ማሸነፍ ችለዋል፡፡

ድሉን ተከትሎ ኤቷል ከፉስ ራባት ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ ማድረግ ችሏል፡፡ አሃሊ ትሪፖሊ ሶስቱንም የምድብ ጨዋታዎች በመሸነፉ የማለፍ ተስፋው ከወዲሁ የጠበበ ነው፡፡

ዛሬ በቤጃያ ከተማ አልጄሪያ ላይ በምድብ አንድ የሚገኙት ኤምኦ ቤጃያ እና ቲፒ ማዜምቤ ይጫወታሉ፡፡ በምድቡ እስካሁን ሽንፈትን ያልቀመሱት ሁለቱ ክለቦች የመሃከላቸው የሁለት ነጥብ ልዩነት አለ፡፡ ቤጃያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ሲሆን ይህንን ጨዋታ በማሸነፍ ከማዜምቤ የመሪነቱን በትር ለመረከብ ይፈልጋል፡፡ ቲፒ ማዜምቤ በ2016 ወደ ሰሜን አፍሪካ ተጉዞ ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች በሽንፈት የደመደመ ሲሆን የምድቡን መሪነት ለማጠናከር ቤጃያን ማሸነፍ ወይም ነጥብ መጋራት ግድ ይለዋል፡፡

 

የቅዳሜ ውጤቶች

ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) 1-1 ሚዲአማ (ጋና)

ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) 3-0 አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ)

ዕሁድ ሃምሌ 10/2008

20፡45 – ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ) ከ ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) (ስታደ ዩኒት መግሪቢን)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *