በቀጣዩ የውድድር ዘመን ከሀዋሳ ከተማ ጋር ለመዝለቅ የወሰኑት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በክረምቱ እምብዛም ገብያው ላይ እንደማይሳተፉ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል፡፡
ክለቡ በአሁኑ ወቅት ውል የማደስ ድርድሮች እያከናወነ ሲሆን በሚለቁት ምትክ ጥቂት ተጫዋቾች እንደሚያስፈርም ታውቋል፡፡ በዚህም አስጨናቂ ሉቃስ ፣ ግሩም አሰፋ እና ዮሐንስ በዛብህ ውላቸውን ለማደስ ተቃርበዋል፡፡
በዘንድሮ ውድድር ዘመን የአንድ አመት ውል በመፈራረም ክለቡን ተቀላቅሎ ቁልፍ ተጨዋች መሆን የቻለው አስቻለው ግርማ ከክለቡ ጋር እየተደራደረ ሲሆን በቅርቡ ከስምምነት ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አሁን በተሰራጨው ዜና ደግሞ አስቻለው ግርማ የቀድሞ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡናን መቀላቀሉ ተረጋግጧል፡፡
በሌላ በኩል ሙጂብ ቃሲም ለውል ማደሻው በቀረበለት ሂሳብ ባለመስማማቱ ክለቡን ሊለቅ እንደሚችል ታውቋል፡፡ ጠንካራው ተከላካይ በቀጣዩ አመት በክለቡ እንደሚቆይ አሰልጣኝ ውበቱ ቢተማመኑም ሙጂብ ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ ከደደቢት እና አዳማ ከተማ ድርድር ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ቀጣይ ማረፈያውም አዳማ ከተማ እንደሚሆን እርግጥ እየሆነ መጥቷል፡፡
ሌላው ክለቡን እንደሚለቅ የሚጠበቀው አጥቂው በረከት ይስሃቅ ነው፡፡ በረከት ደደቢትን ለቆ ዘንድሮ ወደ ሀዋሳ ከተመለሰ ወዲህ በውድድር አመቱ እጅግ ጥቂት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን በዚህ ክረምት ወደ ሌሎች ክለቦች ያቀናል ተብሏል፡፡
በተያያዘ ዜና ዩጋንዳዊው አማካይ ሀምዛ ኦሌማ በሀዋሳ ከተማ እንደሚፈለግ በዩጋንዳ ድረ-ገፆች የተሰራጨው ዜና ሀሰት መሆኑንና ክለቡ ስለተጫዋቹ ምንም አይነት መረጃ እንደሌለው አሰልጣኝ ውበቱ አረጋግጠዋል፡፡