የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎችን ሳይጨምር የ5 ሳምንታት እድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡ በሁለቱም ምድብ የሚገኙት ቀዳሚ ሁለት ክለቦችም ወደ ፕሪሚር ሊግ የሚያደርጉትን ጉዞ አሳምረዋል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚደረገውን ግስጋሴ እና ወደ ብሄራዊ ሊግ ላለመውረድ የሚደረገውን ትንቅንቅ በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡
ምድብ ሀ
ወሳኙ የ26ኛ ሳምንት ፍልሚያ
በ26ኛው ሳምንት ፋሲል ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት ጨዋታ ከምድቡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያልፉ ሁለት ክለቦችን የመለየት አቅም ያለው ነው፡፡ ፋሲል ከተማ ጨዋታውን ካሸነፈ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መግባቱን ሲያረጋግጥ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርትን የሚገጥመው ወልድያም 3 ነጥብ ይዞ ከተመለሰ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለሱን ያረጋግጣል፡፡
ሁለተኛው ዙር የፈጠረው ልዩነት
የከፍተኛ ሊጉ 1ኛ ዙር ሲጠናቀቅ ክለቦች አንገት ለአንገት ተናንቀው ማን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንደሚያልፍ ፍንጭ ለመስጠት አዳጋች ሆኖ ነበር፡፡ የ2ኛው ዙር ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ተጉዟል፡፡ ፋሲል ከተማ እና ወልድያ በወጥ አቋማቸው ዘልቀው መሪነቱ ላይ በመፈራረቅ ጉዟቸውን ሲያሳምሩ ከመሪዎቹ ተርታ የነበሩት መቐለ ከተማ ፣ አማራ ውሃ ስራ እና ዘግይቶ መሪዎቹን የተቀላቀለው ኢትዮጵያ መድን ከሁለቱ መሪዎች ጋር በእኩል ፍጥነት መጓዝ ተስኗቸዋል፡፡
ለንፅፅር በመጀመርያው ዙር እና አሁን ያለውን የነጥብ ልዩነት ይመልከቱ፡-
ያለመውረድ ትንቅንቅ
ከዚህ ምድብ ሁለት ክለቦች ወደ ብሄራዊ ሊጉ የሚወርዱ ሲሆን ከ10ኛ ደረጃ በታች የሚገኙ ክለቦች የመውረድ ስጋት አለባቸው፡፡ እስከውድድር ዘመኑ አጋማሽ ድረስ ግርጌውን ይዘው የቆዩት ሰሜንሸዋ ደብረብርሃን እና አክሱም ከተማ ቢሆኑም የኋላ ኋላ በርካታ ክለቦች ያለመውረድ ፉክክሩን ተቀላቅለዋል፡፡ በተለይም በመጀመርያዎቹ ተከታታይ 8 ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናገድ መልካም አጀማመር አድርጎ የነበረው ወሎ ኮምቦልቻ በሁለተኛው ዙር እጅግ ተዳክሞ ከወራጅ ቀጠናው ያለው ርቀት የ5 ነጥብ ብቻ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ አዲስ አበባ ፖሊስ በተከታታይ 4 ጨዋታ አሸንፎ ግሩም አጀማመር ቢያደርግም ከ6 ወራት በኋላ ራሱን ከወራጅ ቀጠናው በ3 ነጥቦች ልዩነት አግኝቷል፡፡
ምድብ ለ
ይህ ምድብ ከምድብ ሀ አንፃር እምብዛም ፉክክር ሳይታይበት ዘልቋል፡፡ በኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክንያት የጅማ አባ ቡና እና አአ ከተማ ጨዋታዎች ወደ ሌላ ጊዜ ባይተላለፉ ኖሮ ሁለቱ ክለቦች ቀደም ብለው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መግባታቸውን ሊያተጋግጡ ይችሉ ነበር፡፡ ያም ሆኖ 3 ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ጅማ አባ ቡና እጅግ የተሳካ አመት አሳልፎ በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ጅማን ለመወከል ከጫፍ ደርሷል፡፡ አባ ቡና በ26ኛው ሳምንት ድል ከቀናው እና ወራቤ ከተማ ከተሸነፈ 7 ጨዋታዎች በእጁ ላይ እየቀሩት ሊጉን መቀላቀሉን ያረጋግጣል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አልፎ አልፎ የሚዋዥቅ አቋም ቢያሳይም ተከታዮቹን በጊዜ መራቁ ጥቅም ሰጥቶታል፡፡ ወራቤ ከተማ በሁለተኛው ዙር አስፈሪ ግስጋሴ በማድረግ አዲስ አበባን ቢጠጋውም ቅዳሜ እለት እርስ በእርስ ያደረጉት ጨዋታን አዲስ አበባ በማሸነፉ ልዩነታቸው ወደ 6 ሰፍቷል፡፡ አዲስ አበባ ከ ወራቤ በተሻለ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች የሚኖሩት መሆኑን ከግምት ስናስገባ የወራቤ ተስፋ እየጨለመ መሆኑን እንረዳለን፡፡
ያለመውረድ ትንቅንቅ
እንደ ምድብ ሀ ሁሉ ከዚህ ምድብም ሁለት ቡድኖች ወደ ብሄራዊ ሊግ ይወርዳሉ፡፡ የውድድር አመቱን ሙሉ ወራጅ ቀጠናው ውስጥ የዳከሩት ፌዴራል ፖሊስ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥቂቱ ቢያንሰራሩም ከሌሎቹ ክለቦች በነጥብ ወደ ኋላ ቀርተዋል፡፡ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ባቱ ከተማ ከቀጠናው በ4 ነጥብ ብቻ በመራቁ ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ በሶስቱ ክለቦች መካከል ይመስላል፡፡