የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን የሆነው ደደቢት ዛሬ በአአ የጎልፍ ክለብ ባካሄደው ስነስርአት ለቡድኑ አባላት ሽልማት አበርክቷል፡፡
በስነ ስርአቱ መጀመርያ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ቡታ የውድድር ዘመኑን የደደቢት ሴቶች ቡድን ጉዞ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በመቀጠል ክለቡ ያገኛቸውን ዋንጫዎች በአምበሎቹ አማካኝነት ለክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ወልዳይ በርኸ አስረክበዋል፡፡ በዞኑ ውድድር የተገኘውን ዋንጫ 2ኛ አምበሏ ወይንሸት ጸጋዬ ስታስረክብ በማጠቃለያው የተገኘውን ዋንጫ ደግሞ ዋና አምበሏ ኤደን ሽፈራው አስረክባለች፡፡
በመቀጠል በማጠቃለያ ውድድር ኮከብ ሆነው ያጠናቀቁት ኮከብ ግብ ጠባቂዋ ሊያ ሽብሩ ፣ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዋ ሎዛ አበራ እና ኮከብ አሰልጣኙ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከክለቡ የቴክኒክ ዳይሬክተር አስራት ኃይሌ እጅ ተረክበዋል፡፡
ከርክክቡ በኀላ ለቡድኑ አባላት የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ከ20 ሺህ ብር ጀምሮ በየደረጃው ሽልማት ተበርክቷል፡፡ ክለቡ ከሸለመው በተጨማሪ ጉና ንግድ ለቡድኑ አባላት ከ15 ሺህ ብር ጀምሮ በየደረጃው ሽልማት አበርክቷል፡፡
ብርቱካን ገብረክርስቶስ ደግሞ ልዩ ተሸላሚ በመሆን ተጨማሪ 5ሺህ ብር ተበርክቶላታል፡፡
ከሽልማት ስነስርአቱ በመቀጠል ተጫዋቾቹ ያዘጋጁትን ስጦታ በአምበሏ ኤደን ሽፈራው አማካኝነት ለፕሬዚዳንቱ አቶ ወልዳይ አበርክተዋል፡፡
ሎዛ አበራ ፣ ፍሬው ሃይለ ገብርኤል ፣ ሊያ ሽብሩ እና ኤደን ሽፈራው ከሽልማቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር ለስኬታቸው የክለቡን አስተዳደር እና ደጋፊዎች አመስግነዋል፡፡ በመጨረሻም አቶ ወልዳይ በርኸ የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል፡፡