” ይህ ስኬት በአሰልጣኝነት ታሪኬ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው ” የፋሲል ከተማ አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 26ኛ ሳምንት ጨዋታ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያልፍ አንድ ቡድን ለይቷል፡፡ ፋሲል ከተማ መድንን 1-0 ካሸነፈ በኋላም ከረጅም ጥበቃ በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አድጓል፡፡

የክለቡ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድናቸው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መግባቱን ካረጋገጠ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስኬቱ በአሰልጣኝነት ህይወታቸው ትልቁን ቦታ የሚይዝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

” ባለፉት አራት እና አምስት አመታት ከተለያዩ ክለቦች ጋር አልፌያለው፡፡ ትናንት ያሳካሁት ውጤት ግን በአሰልጣኝነት ታሪኬ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ስኬት ነው፡፡ በህይወቴ ትልቁ የደስታ እና የተለየ ስሜት የተሰማኝ ቀን ነው፡፡ ” ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ዘማርያም ቡድናቸው ወጥ አቋም በማሳየቱ አድካሚውን የውድድር ዘመን በስኬት ማጠናቀቁ እንደሚገባው ገልጸው የስኬታቸውን ምስጢር ያብራራሉ፡፡

” በጣም ጥሩ የውድድር አመት ነበር፡፡ በአመቱ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ካሳየነው  ጥሩ አቋም አንፃር ከዚህ ምድብ ማለፋችን ይገባናል፡፡

” ውድድሩ በጣም አድካሚ ነው፡፡ ከነበረው ክለብ ብዛት እና መርሃግብር አወጣጥ አንጻር ካየነው ከባድ ነበር፡፡ ያም ቢሆን ፈጣሪ ይመስገን ለዚህ በቅተናል፡፡

” ዘንድሮ በተለይ ሁለተኛው ዙር ላይ ወጥ አቋም ለማሳየታችን በተጫዋቾቼ መካከል የነበረው ህብረት ፣ አንድነት ፣ ፍቅር እና የማሸነፍ ስሜታቸው እንዲሁም በሜዳችንም ሆነ ከሜዳ ውጪ ሁሉም የኛ ሜዳ ነው ብሎ በማሰብ መጫወታችን ረጅም ርቀት እንድንሄድ አድርጎናል፡፡ ” ሲሉ የቡድናቸው የአሸናፊነት መንፈስ ለስኬታቸው ጉልህ ድርሻ እንዳበረከተ ገልጸዋል፡፡

PicsArt_1469086935416

አሰልጣኙ ከቡድናቸው ጥንካሬ በተጨማሪ የፋሲል ከተማ ልዩ መገለጫ የሆነው ደጋፊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

” ደጋፊው ልዩ ነው፡፡ በቃ በሄድንበት ቦታ ሁሉ በብዛት ነው ነው የሚመጡት፡፡ ትናንት ደግሞ የድጋፍ አሰጣጡ ልዩ ነበር፡፡ መንገዱ በባንዲራ አሸብርቆ ከተማው ቀይና ነጭ ሆኖ ነበር፡፡ ሜዳውም የነበረው ድምቀት ልዩ ነበር፡፡ በቃ ያለ እነሱ የትም መድረስ አንችልም ነበር ፤ ለእነሱ ከፍተኛ ዋጋ ነው የምንሰጣቸው ፤ አስተዋፆአቸው ከፍተኛ ነበር፡፡ ”

በመጨረሻም ስለቀጣዩ አመት ሀሳባቸው ገልጸው አስተዳየታቸውን አጠናቀዋል፡፡

” አሁን አላማችን የነበረው ከምድቡ ማለፍ ነበር ፤ ይህን አሳክተናል፡፡ ከአሁን በኋላ በሊጉ ለመፎካከር የምንሰራ ይሆናል፡፡ እርግጥ በአሁን ሰአት ያሉት አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ጥሩ አቋም ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ማስተካከል የሚገቡን ነገሮች ስላሉ ወደ ገብያውም ገብተን ቡድናችንን የማጠናከር ስራ እንሰራለን፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *