ደደቢት ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያልፍ መከላከያ ወደቀ

በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ እየተሳተፉ የሚገኙት ደደቢት እና መከላከያ ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናግደዋል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም በርካታ ተመልካች በተከታተለው የመከላከያ እና አኤፍሲ ሊዮፓርድስ ጨዋታ መከላከያ በገዛ ሜዳው ተሸንፎ ከውድድር ወጥቷል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ሲቀሩት ሚካኤል ደስታ ከቅጣት ምት ያሸገረው ኳስ ማንም ሳይነካት ወደጎልነት ተቀይራ የመጀመርያው አጋማሽ በመከላከያ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡ በ2ኛው አጋማሽ የበለጠ ጫና ፈጥረው ተጨማሪ ግብ ያክላ ተብሎ ቢጠበቅም በእለቱ የመከላከያ ተከላካዮችን ሲረብሽ የዋለው አለን ዋንጋ በ48ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ የጦሩን ህልም አጨልሞታል፡፡ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ለግቧ መቆጠር ተጠያቂ ሁኗል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ጫና መፍጠር የተሳናቸው መከላከያዎች በሚካኤል ደስታ ፣ አማኑኤል ግደይ እና ሙሉአለም ጥላሁን አማካኝነት በተደጋጋሚ ከርቀት ቢሞክሩም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር አልቻሉም፡፡

የጨዋው መደበኛ ሰአት ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው አለን ዋንጋ የሊዮፓርድስን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ያረጋገጠች ግብ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ጨዋታው በናይሮቢው ክለብ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በድምር ውጤት 4-1 አሸንፎ ወደ ተከታዩ ዙር ያለፈው ሊዮፓርድስ በ1ኛው ዙር የደቡብ አፍሪካውን ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ይገጥማል፡፡

አዲስ አበባ ላይ እጅግ በርካታ ግቦችን አምክኖ 3-0 ያሸነፈው ደደቢት ወደ ዛንዚባር ተጉዞ ለጥቂት ከውድድሩ ከመውጣት ተርፎ ተመልሷል፡፡ የዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም በመጀመርያው ጨዋታ እጅግ ተዳክሞ በመቅረቡ በመልሱ ጨዋታ ምንም አይፈጥርም ቢባልም ሰማያዊውን ጦር 2-0 አሸንፏል፡፡

በድምር ውጤት 3-2 አሸንፎ ወደ ተከታዩ ዙር ያለፈው ደደቢት ቀጣይ ተጋጣሚው የ3013 የአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊው የቱኒዚያው ሴፋክሲያን እንደመሆኑ የቻምፒዮንስ ሊግ ጉዞው በፈተና የተሞላ ያደርግበታል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ