በኢትየጵያ ከ17 አመት በታች የማጠቃልያ ውድድር 8ኛ ቀን ውሎ በተደረጉ ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ድል ሲቀናው ሲዳማ እና ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
08:00 ላይ ሀዋሳ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 2-0 በማሸነፍ የማለፍ ተስፋውን አስፍቷል፡፡ የሀዋሳን የድል ጎሎች ገብረመስቀል ደበሌ እና ያሬድ መሀመድ አስቆጥረዋል፡፡
10:00 ላይ በተካሄደው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና ካለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡
የዚህ ምድብ አላፊ እስካሁን ያልተለየ ሲሆን ወደ ግማሽ ፍጻሜ የሚያልፉትን ክለቦች ለመለየት የመጨረሻውን ጨዋታ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
በተያያዘ ዜና ትላንት የተካሄደው የኢትዮዽያ ንግድ ባንክ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ከስፖርታዊ ጨዋነት መርህ ውጪ የዕለቱ ዳኞች ላይ በፈፀሙት ያልተገባ ባህሪ ምክንያት ሦስት የኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ተጨዋቾች ላይ ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡ ውሳኔው የተላለፈው በፍርዱ ተካልኝ ፣ ሄኖክ ሩጋ እና ምስክር ታገል ላይ ሲሆን የአንድ አመት ቅጣትና የ5000 ብር የገንዘብ ቅጣት በዲሲፒሊን ኮሚቴው ተወስኖባቸዋል፡፡
ውድድሩ ነገ ሲቀጥል በምድብ ለ የመጨረሻ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 04:00 ላይ አዳማ ከ ወላይታ ድቻ (ወንጂ ሜዳ) እንዲሁም መከላከያ ከ ኢትዮጵየያ ንግድ ባንክ (አዳማ አበበ በቂላ ስታድየም) ይጫወታሉ፡፡