ቅዳሜ ፤ ሐምሌ 16 ቀን 2008
የዳዋ ሁቴሳ ማረፍያ አዳማ ከተማ ሆኗል
አዳማ ከተማ ዳዋ ሁቴሳን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሷል፡፡ ዳዋ በ2006 ክረምት ናሽናል ሴሚንትን ለቆ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀለ ወዲህ በመደበኛነት መጫወት የተሳነው ሲሆን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ክለቡን እንደሚለቅ ሲጠበቅ ነበር፡፡
አዳማ ዳዋ ሁቴሳን ጨምሮ ሙጂብ ቃሲም ፣ ኤፍሬም ቀሬ ፣ ኄኖክ ካሳሁን እና ጥላሁን ወልዴን በማስፈረም ስብስቡን ከወዲሁ እያጠናከረ ይገኛል፡፡
አበበ ጥላሁን እና ትርታዬ ደመቀ የዘንድሮ ተረኞች?
ሲዳማ ቡና የአርባምንጭ ከተማዎቹን ትርታዬ ደመቀ እና አበበ ጥላሁንን ለማስፈረም እንደተስማማ ተሰምቷል፡፡
ድንቅ የውድድር አመት ያሳለፈው ተከላካዩ አበበ ጥላሁን የአንተነህ ተስፋዬን ክፍተት በሚገባ የሸፈነ ሲሆን አሁን ደግሞ በሲዳማ አጣማሪው ለመሆን ከይርጋለሙ ክለብ ጋር በቃል ደረጃ መስማማቱ ተነግሯል፡፡
ሲዳማ ቡና በ2006 ክረምት እንዳለ ከበደን ፣ በ2007 ክረምት ሙሉአለም መስፍን ፣ አንተነህ ተስፋዬ እና አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህን ከአርባምንጭ ያስኮበለለ ሲሆን የዘንድሮው ተረኞች ደግሞ ትርታዬ እና አበበ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሀዋሳ ከተማ ያሬድ ዝናቡ እና ወንድሜነህ አይናለምን ለማስፈረም ተቃርቧል
ሀዋሳ ከተማ የደደቢቱ አማካይ ያሬድ ዝናቡ እና የደቡብ ፖሊሱ ግብ አዳኝ ወንድሜነህ አይናለምን በእጁ ለማስገባት መቃረቡ ታውቋል፡፡
ያሬድ ዝናቡ ደደቢትን የለቀቀ ሲሆን ለሀዋሳ ከፈረመ ከቀድሞ አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ጋር በድጋሚ ይገናኛል፡፡
ሌላው ለሀዋሳ ከተማ ለመፈረም ከስምምነት እንደደረሰ እየተነገረ የሚገኘው ወንድሜነህ አይናለም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከፍተኛ ሊግ ድነንቅ አቋሙን በማሳየት ላይ የሚገኝ ሲሆን 17 ግቦች ማስቆጠር ችሏል፡፡ አጥቂ አማካይነት እና አጥቂነት ተሰልፎ መጫወትም ይችላል፡፡
ወንድወሰን ሚልኪያስ ወደ አርባምንጭ
አርባምንጭ ከተማ የአዳማው ወንድወሰን ሚልኪያስን በእጁ አስገብቷል፡፡
ወንድወሰን በጉዳት ጥሩ የውድድር ዘመነ ያላሳለፈ ሲሆን በአዳማ ኮንትራታቸው ካልታደሰላቸው ተጫዋቾች አንዱ ነበር፡፡
በሌላ በኩል የደደቢቱ የቀኝ መስመር ተከላካይ ተካልኝ ደጀኔ ወደ አርባምንጭ ከተማ ለማምራት መቃረቡን ከወደ አርባምንጬ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ዋልያዎቹ የመጨረሻ ማጣርያ ጨዋታቸውን ሀዋሳ ላይ ያደርጋሉ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቀጣዩ ወር መጨረሻ ከሲሸልስ ጋር የሚያደርገው የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም ይደረጋል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ ዋንኛ ሜዳ የሆነው አዲስ አበባ ስታድየም በተደራራቢ ጨዋታዎች እና ዝናብ ከጥቅም ውጪ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በሜዳው ላይ መለስተኛ ጥገና በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ጨዋታውን በሀዋሳ ለማድረግ ለካፍ ጥያቄዋን ማቅረቧን ተከትሎ የሴካፋ የምድብ ውድድሮችን ያስተናገደውን ስታድየም ለማካሄድ ፍቃድ መስጠቱ ታውቋል፡፡
ደደቢት የሎዛ አበራን ውል አድሷል
ደደቢት በመጨረሻም የሎዛ አበራን ኮንትራት ለተጨማሪ ሁለት አመታት አድሷል፡፡
በ2006 ክረምት ሀዋሳ ከተማን ለቃ ደደቢትን የተቀላቀለችው ሎዛ በ2 የውድድር ዘመናት ብቻ 90 የሊግ ግቦች በማስቆጠር የሴቶች እግርኳስ ክስተትነቷን አስመስክራለች፡፡
ደደቢት የመስከረም ካንኮ ፣ አልፊያ ጃርሶ እና ሰናይት ባሩዳን ጨምሮ የአብዛኞቹ ተጫዋቾችን ውል ያደሰ ሲሆን ኤደን ሽፈራውና ሰናይት ቦጋለ እስካሁን ውል ያላደሱ ተጫዋቾች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ብርሃኑ ባዩ ለከርሞ በኤሌክትሪክ ይቆያሉ
ከሊጉ ለመውረድ ለጥቂት የተረፈው ኤሌክትሪክ የአሰልጣኙ ብርሃኑ ባዩን ኮንትራት አድሷል፡፡ አሰልጣኙ ከደካማው የውድድር ዘመን ፍጻሜ በኀላ ሊሰናበቱ እንደሚችሉ ቢነገርም ለከርሞ በቀዮቹ ቤት እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል፡፡
ኤሌክትሪክ በተጫዋቾች ዝውውር ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የማይገኝ ሲሆን አሰልጣኙ ለማስፈረም ያሰቧቸው አዳዲስ ተጫዋቾች እና ኮንትራታቸውን እንዲያድሱ የሚፈልጓቸው ተጫዋቾችን ለክለቡ ቦርድ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስት ተጫዋቾች ላይ አነጣጥሯል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን የሀዋሳ ከተማዋ አማካይ አዲስ ንጉሴ ፣ የሲዳማ ቡናዋ የካቲት መንግስቱ እና የዳሽን ቢራዋ አጥቂ ሄለን እሸቱን ለማስፈረም ድርድር እንደጀመረ ታውቋል፡፡ ስሟ ከደደቢት ዝውውር ጋር የተያያዘው ብሩክታዊት ግርማም በክለቡ የሚያቆያትን ውል ለማደስ በድርድር ላይ እንደምትገኝ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡