ዛምቢያ 2017፡ ለአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ያለፉ ሃገራት ታውቀዋል

ዛምቢያ ለምታስተናግደው የቶታል አፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ያለፉ ሰባት ሃገራት በሳምንቱ መጨረሻ በተደረጉ የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ተለይተዋል፡፡

በማጣሪያው ያልተጠበቁ ሃገራት ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሲጓዙ በወጣቶች የአህጉሪቱን እግርኳስ የተቆጣጠሩት ናይጄሪያ እና ጋና ከውድድሩ ተሰናብተዋል፡፡

ሱዳን ወደ ሌጎስ አምርታ ናይጄርያን 4-3 በማሸነፍ ለአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫው አልፋለች፡፡ ኦምዱሩማን ላይ ናይጄሪያ ሱዳንን 2-1 በማሸነፏ ግምቶች ለፍላይንግ ኢግልሶቹ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሱዳን ናይጄሪያን ከሜዳዋ ውጪ መርታት ችላለች፡፡ ሳሙኤል ቹኩዚ፣ ፈንሶ ባምግቦይ እና ኦርጂ ኦኮንኮ ለባለሜዳዎቹ ከመሸነፍ ያላዳኑ ሶስት ግቦች ሲያስቆጥሩ ካሊድ አብደልሞኔን ኦስማን (3) እና አምጃድ ኢስማኤል የሱዳንን የድል ግቦች አስቆጥረዋል፡፡

ናይጄሪያ ከ2005 ጀምሮ ያለማቋረጥ የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ያለፈች ሲሆን በ63ኛው ደቂቃ የዋለልዲን ሙሳ በቀይ ካርድ መውጣትን ተከትሎ በአስር ተጫዋች መጫወት የተገደደችውን ሱዳን መርታት አቅቷት ከውድድሩ ወጥታለች፡፡

በ2015 ሴኔጋል ባስተናገደችው የ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሻምፒዮን የነበረችው ናይጄሪያ በ2017ቱ ውድድር አናያትም፡፡

ጋና በሜዳዋ ሴኔጋልን 1-0 ማሸነፍ ብትችልም ዳካር ላይ የደረሰባትን የ3-1 ሽንፈት ሳትቀለብስ ቀርታለች፡፡ ቻርለስ ቦአቴንግ የብላክ ሳተላይቶች የድል ግብ በመጀመሪያው አጋማሽ አስቆጥሯል፡፡

ኢትዮጵያን በመጀመሪያው የማጣሪያ ዙር 5-2 በሆነ አጠቃላይ ውጤት መርታት የቻሉት ጋናዎች ከ2009 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ አይጓዙም፡፡

ግብፅ አንጎላን ሉዋንዳ ላይ 4-0 በመርመረም የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋን አረጋግጣለች፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ አንጎላን 1-0 መርታት ለቻለችው ግብፅ የድል ግቦቹን ካሪም ዋሊድ፣ አህመድ ረመዳን (ሁለት) እና አህመድ ያስር ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

image-0-02-01-f2abe3f66e4200e09a839072375e74821b839e23bdf7c1fe4727c51ed4170e13-V

ደቡብ አፍሪካ ሌሶቶን በአጠቃላይ ውጤት 5-0 በማሸነፍ ለአፍሪካ ዋንጫ ትኬቷን ቆርጣለች፡፡ ብሎምፎንቴን ላይ በተደረገው ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ 3-0 ስትረታ ሊያም ጆናታን፣ ሲቦንጋኮንኬ ንቱቱኮ እና ዛማ ራምቡዋኔ ሶስቱን ግቦች አስገኝተዋል፡፡

ጊኒ ጋምቢያን 2-1 ስታሸንፍ ማሊ ቡርኪናፋሶን 2-0 በመርታት ወደ ዛምቢያ ማምራታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ካሜሮን ሊቢያን በአጠቃላይ ውጤት 3-1 በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፈች ሌላኛው ሃገር ነች፡፡

ዛምቢያ ውድድሩን በሁለት ስታዲየሞች በየካቲት 2017 የምታሰናዳ ሲሆን ግማሽ ፍፃሜውን የሚቀላቀሉ አራት ሃገራት በደቡብ ኮሪያ አስተናጋጅነት በ2017 ለሚካሄደው የፊፋ የአለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ የሚያልፉ ይሆናል፡፡

 

ውጤቶች፡

ጋና 1-0 ሴኔጋል (1-3)

ናይጄሪያ 3-4 ሱዳን (2-1)

አንጎላ 0-4 ግብፅ (0-1)

ጊኒ 2-1 ጋምቢያ (0-0)

ማሊ 2-0 ቡርኪናፋሶ (0-0)

ደቡብ አፍሪካ 3-0 ሌሶቶ (2-0)

ሊቢያ 1-0 ካሜሮን (1-3)

 

ተሳታፊ ሃገራት

ዛምቢያ (አዘጋጅ)፣ ሴኔጋል፣ ማሊ፣ ጊኒ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ሱዳን እና ካሜሮን

Leave a Reply