ኮንፌድሬሽን ካፕ፡ አሃሊ ትሪፖሊ ከምድብ ሲሰናበት ያንጋ የማለፍ ተስፋውን አጨልሟል

የኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የምድብ ጨዋታዎች አራተኛ መርሃ ግብር ትላንት ሲደረጉ ኤቷል ደ ሳህል እና ሚዲአማ ወሳኝ ድሎችን አስመዝግበዋል፡፡

ሚዲአማ ያንግ አፍሪካንስን 3-1 በመርታት ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያደርገው ጉዞ አሳምሯል፡፡ በኢሲፖንግ ስፖርትስ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የጨዋታ የበላይነት የነበራቸው ሲሆን ዳንኤል አሞሃ ከማዕዘን የተሻገለትን ኳስ ተጠቅሞ ሚዲአማን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ማሊክ የጋና ኤፍኤ ካፕ አሸናፎዎቹን መሪነት በፍፁም ቅጣት ምት የሚያጠናክር ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ሲቀር አባስ መሃመድ መረነቱን ወደ ሁለት በ22ኛው ደቂቃ ማስፋት ችሏል፡፡ የታንዛኒያው ኢንተርናሽናል ሳይመን ሙሱቫ በ25ኛው ደቂቃ ልዩነቱን ወደ አንድ ቢያጠብም በጨዋታው ጥሩ የነበረው አባስ ሶስተኛውን ግብ አክሏል፡፡

ሚዲአማ የምድብ አንድ ሁለተኝነትን ለጊዜው ከኤምኦ ቤጃያ ሲቀበል ያንጋ ከወዲሁ የማለፍ ተስፋውን አጨልሟል፡፡ የያንጋ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ከማዜምቤ እና ቤጃያ ጋር መሆኑ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የማለፉ ነገር ህልም እየሆነ መጥቷል፡፡

PicsArt_1469606641174

አል አሃሊ ትሪፖሊ ከምድብ ሁለት መሰናበቱን ማክሰኞ ምሽት ቱኒዚያ ላይ በገለልተኛ ሜዳ በኤቷል ደ ሳህል ከተሸነፈ በኃላ አረጋግጧል፡፡ በስታደ ቸድሊ ዙተን በተካሄደው ጨዋታ ኤቷል ከምድብ መሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የቻለበት ውጤት አስመዝግቧል፡፡ አህመድ አካያቺ የኤቷልን የድል ግብ በሰባኛው ደቂቃ ከመረብ አሳልፏል፡፡ ኤቷል ሰባት ነጥብ በመያዝ ከመሪው ፉስ ራባት ጋር መስተካከል ችሏል፡፡

የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ ሉቡምባሺ ላይ ቲፒ ማዜምቤ ኤምኦ ቤጃያን ያስተናግዳል፡፡ በሞሮኮ ደርቢም ፉስ ራባት ከካውካብ ማራካሽ ዳግም በወሳኝ ጨዋታ ይገናኛሉ፡፡

 

የማክሰኞ ውጤቶች፡

ሚዲአማ (ጋና) 3-1 ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ)

አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) 0-1 ኤቷል ስፖትቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ)

 

የረቡዕ ጨዋታዎች፡

15፡30 – ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) ከ ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ) (ስታደ ቲፒ ማዜምቤ)

21፡30 – ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ) ከ ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ) (ኮምፕሌክስ ስፖርቲፍ ሞላይ አል ሃስን)

Leave a Reply