ኮንፌድሬሽን ካፕ፡ ቲፒ ማዜምቤ እና ፉስ ራባት ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማለፍ ተቃርበዋል

የኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የምድብ ጨዋታዎች ረቡዕ ቀጥለው ሲደረጉ ቲፒ ማዜምቤ እና ፉስ ራባት አንድ እግራቸውን ወደ ግማሽ ፍፃሜው ያስገቡበትን ድል በሜዳቸው አስመዝግበዋል፡፡

የምድብ አንድ መሪው ቲፒ ማዜምቤ ሉቡምባሺ ላይ ኤምኦ ቤጃያን 1-0 አሸንፏል፡፡ የማዜምቤን የድል ግብ የዛምቢያው ኢንተርናሽናል ሬንፎርድ ካላባ በሁለተኛው አጋማሽ ከመረብ አሳርፏል፡፡

የቤጃያ የፊት መስመር ግቦችን የማስቆጠር አቅሙ በእጅጉ ተዳክሟል፡፡ ክለቡ ባጠቃላይ በአራት የምድብ ጨዋታዎች ያስቆጠረው የግብ መጠን አንድ ብቻ ነው፡፡

ድሉን ተከትሎ ማዜምቤ ከሚዲአማ በአምስት ነጥብ ርቆ መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከቲፒ ማዜምቤ ይልቅ ለሚዲአማ እና ቤጃያ ወሳኝ ናቸው፡፡

ፉስ ራባት የምድብ ሁለት መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል ካውካብ ማራካሽን 3-1 በመርታት አስመዝግቧል፡፡ የሞሮኮው ሻምፒዮን ፉስ ጨዋታው በተጀመረ በ17 ደቂቃዎች ውስጥ 3-0 መምራት የቻለ ሲሆን ካውካብ ማራካሾች ወደ ጨዋታ የመመለስ ጥረታቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ነበር የደበዘዘው፡፡ መሃመድ ናሂሪ (2) እና ኤል መሃዲ ኤል ባሲል ለፉስ ኳስ እና መረብን ሲያገኛኙ ካሊድ ሴካት የካውካብን ማስተዛዘኛ ግብ በጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል አስቆጥሯል፡፡

ድሉን ተከትሎ ፉስ ራባት በአስር ነጥብ የምድቡ መሪ ሲሆን ኤቷል ደ ሳህል በሰባት ይከተላል፡፡ ተሸናፊው ካውካብ ማራካሽ በስድስት ሶስተኛ ነው፡፡

 

የረቡዕ ውጤቶች

ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) 1-0 ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ)

ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ) 3-1 ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ)

Leave a Reply