ስለ ታከለ አለማየው አሳዛኝ ጉዳት ወላጅ አባቱ ይናገራሉ

የአዳማ ከተማው የመስመር አማካይ ታከለ አለማየሁ እሁድ ምሽት በአዳማ በሚገኝ የመዝናኛ ስፍራ በተነሳ ፀብ አይኑ ላይ በጠርሙስ ተወግቶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡

በአሁኑ ሰአት በምኒሊክ ሆስፒታል የህክምና ክትትል በማድረግ ላይ በሚገኘው ታከለ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የተጫዋቹ ወላጅ አባት አቶ አለማየሁ በተፈጠረው ሁኔታ እጅግ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

” በጣም ያሳዝናል፡፡ ታከለ የህዝብ ልጅ ነው ፤ ጉዳት አድራሾቹ ይህንን አልተረዱም፡፡ በልጄ ላይ ይህን ጉዳት ያደረሱት ሰዎች ምን አስበው እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ” ብለዋል፡፡

አቶ አለማየሁ በታከለ ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ የነበረውን ሁኔታና የጉዳት መጠን እንዲህ ያብራራሉ፡፡

” እንግዲህ ጉዳቱ እንዳጋጠመው በቀጥታ ወደ አዳማ ሆስፒታል ነው የወስድነው፡፡ አይኑ በጣም እንደተጎዳና የተጎዳው አይን መውጣት እንዳለበት ሲነገረኝ አይኔ እያየ ይህን ማድረግ እንደማልችልና ወደ አዲስ አበባ ለተሻለ ህክምና ሪፈር እንዲሰጡኝ ጠይቄ ወደ አዲስ አበባ ጉርድ ሾላ እና ዘንባባ ሆስፒታሎች ይዤው ብሄድም እዛም ተመሳሳይ ነገር ነገሩኝ፡፡ ይህንም ባለመቀበል ሚኒሊክ ሆሲፒታል ብወስደውም እዛም ይሄን ሲነግሩኝ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ትላንት በቀጠሮ መሰረት ዶክተሮቹ ተረባርበው የተሳካ ህክምና አድርገውለት አንድ አይኑ ሊወጣ ችሏል፡፡ ”

” በነገው ቀጠሮ ውጤቱ ታውቆ የአይን የንቅለ ተከላ የሚከናወን ይሆናል፡፡ ይህን ህክምና ማድረግ የሚቻለው በሀገር ውስጥ ወይስ በውጭ የሚለውን ምላሽ እንጠብቃለን፡፡ ”

አቶ አለማየሁ አክለውም በልጃቸው ላይ ከደረሰው አደጋ በኋላ ያገዟቸውን አካላት አመስግነው ወደ ጤንነቱ እንዲመለስ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

” የጉዳቱ ወሬ ከተሰማ ጀምሮ ከፍተኛ ድጋፍ ተደርጎልናል፡፡ በተለይ የህክምና ጣቢያ ባለሙያዎች ለዚህም ምስጋና አቀርባለው፡፡

” ታከለ የእኔ የአባቱና የእናቱ ልጅ ብቻ አይደለም የኢትዮዽያ ህዝብ ልጅ ነው ሁሉም የሚወደው የሚያደንቀው የሚያከብረው ልጅ ነው፡፡ ከኢትዮዽያ ህዝብ ጋር በመሆን በተሻለ ህክምና ጤንነቱ እንዲመለስ ከጎናችን እንዲሆኑ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *