ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ለኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ፍፃሜ ደረሱ

የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ ዛሬ በተካሄዱት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችም ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ በመለያ ምቶች አሸንፈው ወደ ፍጻሜው አልፈዋል፡፡

07:00 ላይ መከላከያ ከ ሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ መደበኛ ክፍለ ጊዜ 1-1 ተጠናቋል፡፡

ሲዳማ ቡና በአማኑኤል እንዳለ ጎል ቀዳሚ መሆን ሲችል የእንቅስቃሴ የበላይነት የነበራቸው መከላከያዎች በዮሃንስ ደረጄ ግብ አቻ መሆን ችለዋል፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ለሚመራው ዮሃንስ ይህ ግብ በማጠቃለያው ያስቆጠረው 5ኛ ግቡ ነው፡፡

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 በመጠናቀቁ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች ሲዳማ ቡና 4-3 በማሸነፍ ወደ ፍጻሜው አልፏል፡፡

PicsArt_1469720156944

10:00 ላይ ሀዋሳ ከተማ ከ አዳማ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ እንደመጀመርያው ሁሉ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች አምበሉ ወንድምአገኝ ማዕረግ ባስቆጠረው ግብ ሀዋሳ ከተማ ቀዳሚ መሆን ሲችል ኢሳ ፍቃዱ በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማን አቻ አድርጓል፡፡

የአቻ ውጤቱን ተከትሎ ወደ መለያ ምት ያመሩ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ 4-2 በማሸነፍ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል፡፡

PicsArt_1469719913194

የፍፃሜው ጨዋታ በጎረቤታሞቹ ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ መካከል በመጪው ቅዳሜ 09:00 ላይ ይደረጋል፡፡ ሀዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ማጠቃለያ ለፍጻሜ ከመድረሱ ባሻገር ከ17 አመት በታች ጥሎ ማለፍ ላይም ለፍጻሜ (ከወላይታ ድቻ ጋር) መድረሱ ይታወሳል፡፡

በማጠቃለያ ውድድሩ ከደቡብ-ምስራቅ ዞን የመጡት ቡድኖች የበላይነት የታየበት ሆኗል፡፡ 4 ክለቦች ብቻ ከሚገኙበት ይህ ዞን 3 ክለቦች ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀል ሲችሉ በፕሪሚየር ሊጉም ሆነ ጥሎ ማለፉ ለፍጻሜ የደረሱት ክለቦች በሙሉ ከደቡብ-ምስራቅ ዞን የተገኙ ናቸው፡፡

 

PicsArt_1469720079946

* በፎቶው ላይ እንደምትመለከቱት በመጀመርያው ጨዋታ መጨረሻ የሲዳማ ቡና ተጫዋች በቀጣይ ጨዋታ ለሚያደርገው የሀዋሳ ከተማ ተጫዋች የመጫወቻ ጫማ ሲያውሰው ይታያል፡፡ በፍጻሜው ጫማውን ማን ይጠቀምበት ይሆን?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *