‹‹ትኩረታችን የሴፋክሲያኑ ጨዋታ ነው ›› ዳዊት ፍቃዱ

ባለፈው እሁድ የቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር የዛንዚባሩን ኬኤምኬኤም 3-0 ያሸነፈው ደደቢት ከተጋጣሚው አቅም አንፃር ትኩረት ሊያደርግ የሚገባው በአንደኛው ዙር የሚያገኙት የቱኒዚያው ሴፋክሲያን ላይ እነደሆነ ግብ አዳኙ ዳዊት ፍቃዱ ከሊግ ስፖርት ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጧል፡፡

‹‹ የእሁዱ ድል ለመልሱ ጨዋታም ሆነ ለቀጣዩ ዙር ግጥሚያ ትልቅ መነሳሳት ይፈጥርልናል፡፡ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በእያንዳንዱ ጨዋታ ለተጫዋቾች የሚሰጡት ነፃነትም ውጤታማ አድርጎናል፡፡ በአንደኛው ዙር ከኮንፌድሬሽን ዋንጫ ባለድሉ ሴፋክሲያን ጋር ለምናደርገው ፈታኝ ጨዋታ ዝግጁ ሆነን እንቀርባለን፡፡ ››

ዳዊት ስለ ደደቢት ጥንካሬም ይናገራል፡፡

‹‹ የቡድናችን ጥንካሬ የማሸነፍ መንፈሳችን ጠንካራነት ነው፡፡ ቡድናችን በሚገባ ተዋህዷል ፤ በጨዋታው በርካታ የግብ እድል መፍጠር የቻልነውም በተጫዋቾች መካከል መግባባት ስላለ ነው፡፡ ተከላካዮችን የማስጨነቅ እና በተደጋጋሚ ወደተጋጣሚ የግብ ክልል የመድረስ ብቃታችንም ሌላው ጠንካራ ብቃታችን ነው፡፡ ››

አምና በሊጉ 21 ግቦች አስቆጥሮ የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነት ለጥቂት ማጣቱን እና የጌታነህ ከበደ ሊጉን ለቆ መሄድ ተከትሎ ከሊጉ አውራ አጥቂዎች አንዱ መሆን የቻለው ዳዊት ስለ ራሱ የሚናገራው ነገር አለ፡፡

‹‹ የራሴ ጥንካሬ ብዬ የማስበው ከኳስ እና ያለ ኳስ የተጋጣሚ ተከላካዮችን የማስጨነቅ ችሎታዬ ነው፡፡ የግብ እድሎችን ወደ ግብ በመቀየር ላይ ያለውን ድክመቴን ለማሻሻል ሁልጊዜም እተጋለሁ፡፡››

{jcomments on}

ያጋሩ