በወልድያ ከተማ የተገነባው የሼክ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም ወደ መጠናቀቂያው ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ ስታድየሙን የጎበኘው ባልደረባችን መሀመድ አህመድ ስለስታድየሙ ያሰባሰበውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
መቻሬ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ የተገነባው ይህ ስታድየም የግንባታ ሂደቱ 4 አመት ያህል የፈጀ ሲሆን ከግማሽ ቢልዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ይታመናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ወንበር እና ጣርያ የተገጠመለት ስታድየሙ 25ሺህ ሰዎችን በወንበር የማስተናገድ አቅም አለው፡፡
4 የመልበሻ ከፍሎች እና 2 የማሟሟቂያ ሜዳዎቸ ያሉት ስታድየሙ ከዋናው የእግርኳስ እና አትሌቲክስ ሜዳ በተጨማሪ በውጭኛው ስታድየም ክፍል የዋና ገንዳ ፣ የቅርጫት ኳስ ፣ መረብ ኳስ ፣ እጅ ኳስ እና የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎች እንዲሁም ለ34 ሰዎች የሚሆን የእንግዳ ማረፍያ አካቷል፡፡
ልክ እንደ አዲስ አበባ ስታድየም ሁሉ በዙርያው ከመቶ በላይ የንግድ ሱቆች የተዘጋጀለት አዲሱ የወልድያ ስታድየም የሄሊኮፍተር ማረፍያ ፣ በቂ የመኪና ማቆምያ እና ውብ አረንጓዴ ቦታዎች አሟልቷል፡፡
ወደ ስታድየሙ ውስጠኛ ክፍል ስናመራ ሁለት ግዙፍ ስክሪኖች እንደሚገጠም የታወቀ ሲሆን 2 የቪአይፒ ቦታዎች ተዘጋጅተውለታል፡፡ አንደኛው በመስታውት የተከለለና ለደህንነት አስተማማኝ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ መስታውት የሌለው የቪአይፒ መቀመጫዎች ስፍራ ነው፡፡ በዘመናዊ መንገድ የተሰራ የጋዜጠኞች ክፍል ሲኖረው በአንድ ጊዜ በርካታ ሚድያዎች ጨዋታ በቀጥታ እንዲያስተላልፉ በማሰብ የድምፅ መደበላለቅ እንዳይፈጠር ድምፅ የማያሳልፉ ክፍሎችም ተዘጋጅተውለታል፡፡ በትሪቡን በኩል የኤሌክትሮኒክስ መፈተሻ እንደተገጠመለትም ታውቋል፡፡
ይህ ሙሉ ለሙሉ ወንበር የተገጠመለት ዘመናዊ ስታድየም በመጪው ጥቅምት ወር 2009 እንደሚመረቅ የታወቀ ሲሆን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማለፍ እጅግ ጥቂት እርምጃ ብቻ የቀረው ወልድያ ስፖርት ክለብ የቀጣይ የውድድር ዘመኑን ሙሉ መቀመጫው በክለቡ የማልያ ቀለም ባሸበረቀው ዘመናዊ ስታድየም የሚጫወት ይሆናል፡፡
ከስታድየሙ የውስጥ ገፅታዎች የተወሰኑ ምስሎችን እነሆ ብለናል፡-