ስለ ጅማ አባቡና ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደግ ተጫዋቾቹ ምን ይላሉ?

ጅማ አባ ቡና ትላንት ከወራቤ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በአቺ ውጤት አጠናቆ 5 ጨዋታ እየቀረው ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን አረጋግጧል፡፡

ለቡድኑ ውጤት ማማር ከፍተኛውን ሚና ከተወጡት መካከል አንጋፋው የቡድኑ አምበል ቢንያም ሃይሌ ፣ ጠንካራው ተከላካይ በሃይሉ ፣ ባለ ክህሎቱ አማካይ ዳዊት ተፈራ እና ግብ አዳኙ አሜ መሃመድ በጅማ አባ ቡና ወደ ፕሪሚደር ሊግ ማደግ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

PicsArt_1470147085092

” የዚህ ስኬት አካል በመሆኔ ደስታ ተሰምቶኛል” ቢንያም ኃይሌ

” እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ጅማ አባቡና በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ በመሆኑና እኔም የዚህ ስኬት አካል በመሆኔ ደስታ ተሰምቶኛል ”

ልምዱን ስለማጋራት

” በበርካታ ክለቦች ተጫውቼ ያለፍኩ ተጫዋች ነኝ፡፡ ያ ለክለቡ ጠቅሟል ብዬ አስባለው፡፡ አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ወጣቶች ናቸው፡፡ በጣም ያከብሩኛል ፤ የምላቸውንም ይሰሙኛል ፤ ፈጣሪን አመሰግናለው ያው የምላቸውን ስለሚሰሙኝ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ለወጣት ብሄራዊ ቡድንም የተመረጡት የሚባሉትን ስለሚተገብሩ ነው፡፡ በቡድኑ እና በተጫዋቾቹ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ ”

የስኬት ምስጢር

” በመጀመርያ የፈጣሪ ፍቃድ ነው፡፡ ሲቀጥል ፍቅራችን ፣ መከባበራችን ፣ አንድነታችን እንዲሁም በትልቅ አሰልጣኝ እየተመራን ስራችንን መስራታችን እጅግ ትልቅ ስኬት እንድናሳካ ረድቶናል ”

PicsArt_1470146957308

” የተዋሃደ ቡድን ይዘን በመቅረባችን ወደ ፕሪሚየር ሊግ አድገናል” ዳዊት ተፈራ

” አምና ከነበረን አቋም አንፃር እና አምና ከነበሩት ብዙ ተጨዋች ስላልተቀነሱ የተዋሃደ ቡድን ይዘን በመቅረብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደግ ችለናል፡፡ ”

የስኬት ሚስጢር

” ቡድናችን ውስጥ ፍቅር አለ፡፡ አሰልጣኛችን የሚያሰራንን በጥንቃቄ የምንሰራ በመሆኑ ለዛ ነው ስኬታማ መሆን የቻልነው ”

በግሉ ጥሩ አመት ስለማሳለፉ

” ጥሩ አቋም ላይ እንድገኝ ዋናው ምክንያት ሙያዬን አክብሬ ጠንክሬ በመስራቴ በጅማ አባቡናም ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡

ከጎኔ በመሆን ላገዙኝና ለደገፉኝ ቤተሰቦቼ እንዲሁም ለጅማ አባ ቡና ደጋፊዎች በሙሉ ምስጋናዬን  አቀርባለው፡፡ ”

PicsArt_1470147034042

” ጅማ አባቡና የፈረምኩት ፕሪሚየር ሊግ እንደምንገባ እርግጠኛ ስለነበርኩ ነው” አሜ መሃመድ

” ወደዚህ ክለብ ከመምጣቴ በፊት ብዙ ክለቦች አናግረውኝ ነበር፡፡ ሁሉንም ትቼ እዚህ የመጣሁት አምና ድሬደዋ ላይ ያሳዩትን ብቃት አይቼ በቀጣይ አመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንደሚያድግ አምኜ ነበር የመጣሁት ”

ጥሩ የውድድር አመት ስለማሳለፉ

” በግሌ ጥሩ የውድድር አመት እንዳሳልፍ የረዳኝ አሰልጣኛችን የሚሰጠውን ልምምድ በአግባቡና በትኩረት ስለምሰራ ነው፡፡ የቡድን አጋሮቼ የሚያደርጉልኝ እገዛ እና የአባቡና ደጋፊዎች የሚሰጡኝ ድጋፍም ጥሩ ጊዜ እንዳሳልፍ ረድቶኛል ”

በፕሪሚየር ሊጉ ጎልቶ ስለመውጣት

” ድክመቶች ሊኖሩብኝ ይችላል፡፡ ለቀጣይ አመት ከድክመቶቼ ተምሬ አሻሽዬ ከዘንድሮ አመት በበለጠ ጥሩ እንቅስቃሴ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ”

PicsArt_1470146905143

“እያንዳንዱን ጨዋታ እንደ ፍጻሜ ጨዋታ መጫወታችን ለዚህ አብቅቶናል” በሃይሉ

“ከመጀመርያው ይሄን ነበር የምንፈልገው፡፡ ይህን በማሳካታችን በጣም ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ በእግርኳስ ህይወቴ ከአንድ ቡድን ጋር ወደ ፕሪሚየር ሊግ ስገባ  የመጀመርያዬ ነው፡፡

” እያንዳንዱን ጨዋታ እንደ ፍጻሜ ጨዋታ  ነው  የተጫወትነው፡፡ እዚህ የደረስነውና አብዛኛውን ጨዋታ በድል የተወጣነው ያን በማድረጋችንነው ”

ስለ ቀጣይ አመት

” በቀጣይ በፕሪሚየር ሊግ ከዚህ በፊት አድገው መልሰው እኖደወረዱት ሳይሆን ወደ መጀመርያዎቹ ተርታ ለመሰለፍ ጠንክረን እንሰራለን፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *