ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ጌታነህ ከበደ ለሙከራ ወደ ፖርቹጋል ሊግ መሄዱን ደቡብ አፍሪካው ድህረ-ገፅ ኪክኦፍ ዘግቧል፡፡
አጥቂው የውድድር አመቱን በውሰት በዩኒቨርስቲ ኦፍ ፕሪቶሪያ ያሳለፈ ሲሆን በክረምቱ ከቤድቬስት ዊትስ የተለቀቀ ተጫዋች ነው፡፡
የጌታነህ ወኪል ኢቪካ ስታንኮቪች ለኪክኦፍ በሰጠው አስተያየት የቀድሞው የደደቢት አጥቂ ወደ ፖርቹጋሉ ሲዲ ቶንዴላ ክለብ ለሙከራ ሊጓዝ መሆኑን ነው፡፡ “ጌታነህ የፖርቹጋል ቪዛውን አግኝቷል፡፡ የፖርቹጋሉ ክለብ እሱን ለማየት በጣም ፈልጓል፡፡ ሙከራ እንዲያገኝም ጥሪ ያደረገለት ክለቡ ነው፡፡”
በፖርቹጋል ፔሪሜራ ሊጋ የሚወዳደረው ክለብ ዴስፖርቲቮ ደ ቶንዴላ በ1933 እ.ኤ.አ. የተመሰረተ ሲሆን በ2015/16 የውድድር ዘመን ከመውረድ ለጥቂት ተርፏል፡፡ በቀድሞ የቤኔፊካ እና ኮሎኝ የመሃል ተከላካይ ፒቲት ስር የሚሰለጥነው ቶንዴላ የአጥቂ መስመሩን ማጠናከር ይፈልጋል፡፡ በ2016/17 የፕሪሜራ ሊጋ የመክፈቻ ጨዋታም ቻምፒዮኑን ቤኔፊካ ይገጥማል፡፡
ኢትዮጵያዊን ተጫዋቾች ወደ ፖርቹጋል ለሙከራ ሲጓዙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ዓምና ናትናኤል ዘለቀ እና ሳላዲን ባርጌቾ በቀድሞ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ አመቻችነት በሲዲ ፌሬንሳ የሙከራ ግዜ ያሳለፉ ሲሆን ጥበበኛው የአጥቂ አማካይ ሽመልስ በቀለ ለሃያሉ የፖርቹጋል መዲና ክለብ ስፖርቲግ ሊዝበን ለመፈረም ተቃርቦ ነበር፡፡
ጌታነህ ከወራት በፊት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ለዝውውር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ጥያቄ እንዳቀረቡለት እና ውሳኔውን በክረምቱ የዝውውር መስኮት እንደሚያሳውቅ መናገሩ ይታወሳል፡፡