ጌታነህ ከበደ ወደ ፖርቹጋል የመሄዱን ነገር አስተባብሏል

የዋሊያዎቹ የፊት መስመር ተሰላፊ ጌታነህ ከበደ ወደ ፖርቹጋሉ ሲዲ ቶንዴላ ክለብ ለሙከራ ሊጓዝ ነው ተብሎ በደቡብ አፍሪካው ድህረ-ገፅ ኪክኦፍ የተዘገበው ዘገባ ከእውነት የራቀነው ሲል ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ለእረፍት አዲስ አበባ የሚገኘው አጥቂው ስለፖርቹጋሉ ጉዞ ምንም እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡

“ስለፖርቹጋል ጉዞ ማንም አላናገረኝም፡፡ ወኪሎቼንም ስለተባለው የሙከራ ጊዜ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ እኔ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ወደ ሃዋሳ ተጉዤ የብሄራዊ ቡድን ዝግጅት እቀላቀላለው፡፡ የኪክኦፍ ዘገባ ከእውነት የራቀ ነው::”ሲል ጌታነህ ገልጿል፡፡

ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረገው ፖርቹጋላዊው ወኪል እና የተጫዋቾች መልማይ ማርዮ ቴክሼራ ስለጌታነህ ወደፖርቹጋል ለሙከራ የመምጣቱን ዜና ሃሰት ብሎታል፡፡
“ዜናው ኪክኦፍ ላይ አንብቤዋለሁ፡፡ ጌታነህ ወደ ፖርቹጋል አልመጣም፡፡ የሙከራ ጥሪ በክለቡ በኩል ይላክ አይላክ አሁን ላይ መረጃው የለኝም፡፡ ቶንዴላም ከወዲሁ አጥቂዎችን አስፈርሟል፡፡ ስለዚህ ጌታነህ ወደ ፖርቹጋል ይመጣል የሚል ግምት የለኝም ሲል::” ሃሳቡን አስረድቷል፡፡

እየተደረገ ባለው የብሄራዊ ሊግ ማጠቃልያ ውድድር የትውልድ ከተማውን ክለብ ዲላ ከተማን ለማበረታታት ከሳምንት በፊት ባቱ (ዝዋይ) ላይ የተገኘው ጌታነህ ስለወደፊት ማረፊያው አሁን ላይ አለመወሰኑን ተናግሯል፡፡
“እኔ ከማንም ጋር ስለወደፊት ማረፉዬ አልተነጋገርኩም፡፡ ደቡብ አፍሪካ ይሁን ኢትዮጵያ አሁን ላይ አልወሰንኩም፡፡ ከብሄራዊ ቡድን ጨዋታ በኃላ ውሳኔ ላይ እደርሳለው፡፡”

በውድድር ዓመቱ በግሉ መልካም የሚባል አመትን ያሳለፈው ጌታነህ በዝውውር መስኮቱ መከፈት በኃላ ከቤድቬስት ዊትስ ተለያይቷል፡፡

3 Comments

  1. Hot & resent information from best Media called #Soccer_Ethiopia …………………..tnxs.

Leave a Reply