ማዳጋስካር ለምታስተናግደው የ2017 የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ለማለፍ የመጀመርያ ማጣርያውን ከግብፅ ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ ከ17 አመት ብሄራዊ ቡድን ከ2 ሰአት በኋላ ወደ ግብፅ ይበራል፡፡
የልኡካን ቡድኑ ምሽት 4:45 ላይ ወደ ግብጽ ጉዞውን የሚጀምር ሲሆን ከ 5 ሰአት በረራ በኋላ ካይሮ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን በኩል 20 ተጨዋቾችን ጨምሮ 5 የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ፣ የቡድን መሪው አቶ ልውል ሰገድ በጋሻው ፣ ከፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት አቶ መለሰ ፣ ከቴክኒክ ዲፖርትመት ዳንኤል ገ/ማርያም ወደ ካይሮ አምርተዋል፡፡
ቡድኑን በሀዋሳ ሲያዘጋጁ የከረሙት አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ለጨዋታው እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡
” ከሐምሌ 1 – 24 ድረስ በሀዋሳ ዝግጅታችንን አድርገናል፡፡ በአካል ብቃት ፣ በቴክኒክ ፣ በታክቲክ እና ስነ ልቦና ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ የኢንተርናሽናል የወዳጅነት ጨዋታ ባናገኝም አራት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርገናል፡፡ የተሻለ ጥሩ እንቅስቃሴም አይተናል፡፡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ጨርሰን የግብጹ ጨዋታን እየተጠባበቅን እንገኛለን
” የምንሄደው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ነው፡፡ተጫዋቾቹ ጋር ለሀገር አንድ ነገር ለመስራት ጥሩ ስሜትና ፍላጎት አለ፡፡ እግር ኳስ የሚፈልገውን ሁሉ አድርገን እንመለሳለን” ብለዋል፡፡
አሰልጣኝ አጥናፉ አክለውም ስለተጋጣሚያቸው መረጃ እንደሰበሰቡ ተናግረዋል፡፡
” ከአልጄሪያ ፣ ሱዳን እና ጋቦን ጋር ያደረጓቸውን የወዳጅነት ጨዋታዎች በቪዲዮ አይተናል፡፡ ስለነሱ በቂ ነገር አውቀናል፡፡” ብለዋል፡፡
የኢትየጵያ እና የግብጽ ጨዋታ በመጪው ቅዳሜ በካይሮ ፔትሮ ስፖርት ስታድየም ይካሄዳል፡፡