ብሄራዊ ሊግ ፡ አራዳ ክ/ከተማ እና ለገጣፎ ለፍጻሜው አልፈዋል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ትላንት ተካሂደዋል፡፡

በዝግ ስታድየም በተደረጉት ጨዋታዎች ለገጣፎ እና አራዳ ተጋጣሚዎቻቸውን በመለያ ምቶች በመርታት ለፍፃሜው አልፈዋል፡፡

08:00 በተደረገው ጨዋታ አራዳ ክፍለ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ መደበኛውን ክፍለ ጊዜ 2-2 ተጠናቋል ፡፡ ለአራዳ አብዱለጢፍ ሙራድ እና ሲሳይ ሽፈራው ሲያስቆጥሩ ታደለ አቡኔ እና ታሪኩ ታምራት ለወልቂጤ አስቆጥረዋል፡፡

አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች አራዳ ክፍለ ከተማ 5-4 በማሸነፍ ወደ ፍጻሜው አልፏል፡፡

ከጨዋታው በፊት ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኙ ኤፍሬም ደምሴን ያሰናበተ ሲሆን ጨዋታውንም በረዳት አሰልጣኙ አማካኝነት አድርገዋል፡፡

ክለቡ አሰልጣኝ ኤፍሬምን ለማሰናበቱ የሰጠው ምክንያት የዲሲፕሊን ግድፈት ነው፡፡ አሰልጣኝ ኤፍሬም በበኩሉ አመቱን ሙሉ ሲሰራ እና ክለቡን ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲያሳልፍ ያልተነሳ ጉዳይ አሁን መነሳቱ ምክንያቱን አሳማኝ እንደማያደርገው እና ሆን ተብሎ ለመጉዳት የተደረገ እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡

PicsArt_1470645015899

10:00 ላይ ለገጣፎ ከተማ ከ ሽረ እንዳስላሴ በጨዋታ 1-1 ተለያይተው ለገጣፎ በመለያ ምቶች 4-2 በማሸነፍ ወደ ፍጻሜው አልፏል፡፡

በጨዋታው ፋሲል ቦጋለ የለገጣፎን ግብ ሲያስቆጥር ለሽረ የለገጣፎ ተከላካይ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯል፡፡

የፍጻሜው ጨዋታ ነገ በባቱ ሜዳ የሚካሄድ ሲሆን ቅዳሜ ሊደረግ የነበረው ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመግባት የሚደረገው ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል፡፡

የፍጻሜ ጨዋታ

ማክሰኞ ነሀሴ 3 ቀን 2008

09:00 ለገጣፎ ከተማ ከ አራዳ ክፍለ ከተማ (ባተቱ ሜዳ)

ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመግባት የመለያ ጨዋታ

ሰኞ ነሀሴ 1 ቀን 2008

08:00 መተሃራ ስኳር ከ ካፋ ቡና (ባቱ ሜዳ)

10:00 አማራ ፖሊስ ከ ዲላ ከተማ (ባቱ ሜዳ)

ከውድድሩ ጋር በተያያዘ ዜና አርቢቴር ጌቱ ተፈራ ከክለቦች ጋር ያልተገባ ግንኙነት ሲያደርግ እንደነበር የተደረሰበት በመሆኑ   ከውድድሩ እንዲሰናበት በዳኞች ኮሚቴ ተወስኗል፡፡

Leave a Reply