ማዳጋስካር ለምታስተናግደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ የግብፅ አቻውን ካይሮ ላይ የገጠመው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን 3-1 መርታት ችሏል፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥም በሰሜን አፍሪካ ቡድን ሜዳ ላይ የተመዘገበ ጣፍጭ ድል ሆኖ አልፏል፡፡
ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ቀይ ቀበሮዎቹ አፈግፍገው በመከላከል ተጠምደው ታይተዋል፡፡ በተለይ በጨዋታው የመጀመሪያ 2 ደቂቃዎች ውስጥ ግብፅ ሁለት ግዜ የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል፡፡ እንደአጀማመራቸው ግብ በማስቆጠርም ቅድሚያውን የያዙት ባለሜዳዎቹ ነበሩ፡፡ መሃመድ አብደልጋኒ ግብፅን መሪ የምታደርግ ግብ በ17ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻለው ብሄራዊ ቡድናችን በጫላ ተሺታ ግብ አቻ ችለዋል፡፡ አቡበከር ናስር ከጫላ ተሻገለትን ኳስ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን በ41ኛው ደቂቃ መሪ ማድረግ ችሏል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ግብፅ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወደ ኢትዮጵያ ግብ ክልል በመድረስ የተሸሉ የነበሩ ቢሆንም የፈጠሩት የግብ ማስቆጠር እድል አናሳ ነበር፡፡ አቡበከር የኢትዮጵያን መሪነት ወደ ሶስት የማስፋት እድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በግቡ አናት ላይ በመስደዱ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሚኪያስ መኮንን ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መሪነቱን አስጠብቋል፡፡ ሚኪያስ ሶስት የግብፅ ተከላካዮችን እና ግብ ጠባቂውን በአስደማሚ ሁኔታ በማለፍ ነው የቀይ ቀበሮዎቹን ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር የቻለው፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከግብፁ ብሄራዊ ቴሌቪዢን ጣቢያ ናይል ስፖርት ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ቡድናቸው ጥሩ ጨዋታ እንዳሳየ ተናግረዋል፡፡ “ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ ጥሩ ተጫውተናል፡፡ ይህንንም ሜዳ ላይ ተመልክታችኋል፡፡ ታዳጊዎች የፈለጉት መስራት የሚችሉ ናቸው፡፡ የታክቲክ አረዳዳቸውን ላይ ብቻ ነው አስጨንቆ ልትሰራባቸው የሚገባው፡፡ በመጀመሪያው 20 ደቂቃዎች ተጋጣሚያችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከቶን ነበር፡፡ በጣም ፈጣኖች መሆናቸው ለ20 ደቂቃዎች አስቸግረውን ነበር፡፡ በደካማ ብሄራዊ ብድናች ምክንያት ተጋጣሚያችን ዝቅተኛ ግምት ሰጥቶን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው፡፡ ጥሩ ብቃት እና ጥንካሬ ያላቸውን ልጆች መያዛችን አሸናፊ አድርጓናል፡፡”
ግብፅ በሜዳዋ በሁለቱም ፆታ ኢትዮጵያ ላይ በሜዳዋ የበላይነት ነበራት፡፡ በ1997 ቦትዋና ላይ ተደረገው የአፍሪካ ታዲዎች ሻምፒዮና ላይ ግብፅ ኢትዮጵያን 1-0 በማሸነፍ ሶስተኛ መውጣቷ ይታወሳል፡፡ የሁለቱ ሃገራት የመልስ ጨዋታ ከሁለት ሳምንት በኃላ ይደረጋል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ጨዋታውን ድሬዳዋ ላይ ለማድረግ ያሰበ ቢሆንም የቀይ ቀነሮዎቹ የአሰልጣኞች አባላት ጨዋታው ወደ ሃዋሳ እንዲዛወር ፍላጎት አላቸው፡፡ ፌድሬሽኑ የመልስ ጨዋታው የሚካሄድበትን ሜዳ እንደሚያጤን ተነግሯል፡፡
የጨዋታውን ሃይላይት ይህነን ሊንክ ተከትለው ያገኛሉ፡- You Tube
ፎቶ – ካፍ ኦንላይን