ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ በባቱ እየተካሄደ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፡፡
ውድድሩን ሲከታተሉ የቆዩት የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ድንቅ ብቃታቸውን ሲያሳዩ የነበሩት የካፋ ቡናው ፉአድ ተማም እና የመተሃራ ስኳሩ ዮርዳኖስ ዮሐንስን ለሶስት አመታት አስፈርመዋል፡፡

የበዛብህ መለዮን ኮንትራት ያደሰው ድቻ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በድርድር ላይ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡ ከከፍተኛ ሊግ ተጫዋቾች ሊያስፈርም እንደሚችል ታውቋል፡፡

እንደ ወላይታ ድቻ ሁሉ ድሬዳዋ ከተማም አይኑን በመተሃራ እና ካፋ ቡና ላይ በመጣል ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡
የመተሃራ ስኳሩ ተከላካይ ዘሪሁን አሸንቦ እና የካፋ ቡናው አጥቂ ምንተስኖት ታረቀኝ ለአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን ለ2 አመት የፈረሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ድሬዳዋ ከተማ በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ላይ የሚገኝ ሲሆን ከደቡብ ፖሊስ የመስመር አማካዩ ምስጋናውን ማስፈረም ችሏል፡፡ ምስጋናው ከዘላለም ኢሳያስ እና ሚካኤል ለማ በመቀጠል ለድሬዳዋ የፈረመ 3ኛው የደቡብ ፖሊስ ተጫዋች ሆኗል፡፡