ቻምፒየንስ ሊግ፡ አል አሃሊ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

በቻምፒየንስ ሊጉ ትላንት በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ዜስኮ ዩናይትድ አል አሃሊን ከሜዳው ውጪ ነጥብ አስጥሏል፡፡ ውጤቱ አል አሃሊን አጣብቂኝ ውስጥ ሲከት ዜስኮ ዩናይትድ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያደገውን ጉዞ አመቻችቶለታል፡፡

ሁለት አቻ በተጠናቀቀው ጨዋታ ዜስኮ ዩናይትድ በኬንያዊው ኢንተርናሽናል ጄሲ ዌሬ የአምስተኛ ደቂቃ ግብ ቀዳሚ ሲሆን ተከላካዩ ራሚ ራብያ ከማዕዘን የተሻገረ ኳስን ተጠቅሞ አሃሊ አቻ አድርጓል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ያልተሳካ የሙከራ ጊዜን ያሳለፈው ዌር የዜስኮን ሁለተኛ ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ከመረብ አዋህዷል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የዛምቢያው ክለብ ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥንቃቄ የተካለበት ጨዋታን ቢጫወትም ኢመድ ሞቲብ አሃሊን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

የአቻ ውጤቱ ዜስኮን በስምንት ነጥብ የምድቡ መሪ ሲያደርገው አል አሃሊ በአምስት ነጥብ ሶስተኛ ነው፡፡ የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ አሴክ ሚሞሳስን ማሸነፍ ከቻለ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፍ ይሆናል፡፡

በተያያዘ ዜና ዛሬ ሊካሄድ የነበረው የዛማሌክ እና ኢኒምባ ጨዋታ ለሰኞ ተላልፏል፡፡ ካፍ ጨዋታውን ያለኢኒምባ ዕውቅና ወደ ቅዳሜ አምጥቶት የነበረ ሰሆን የናይጄሪያው ክለብ ቅሬታ አቅርቦ ነበር፡፡ ጨዋታው ለዕሁድ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በዛማሌክ እና ኢኒምባ ጥያቄ መሰረት ወደ ሰኞ ተሸጋሽጓል፡፡

የጨዋታው መራዘም ለኢኒምባ እፎይታ ነው፡፡ በናይጄሪያ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካተው ከስፔን ላሊጋ ክለቦች ጋር የቅድመ-ውድድር ጨዋታ እያካሄዱ የሚገኙት የኢኒምባ ወሳኝ ተጫዋቾች ለዛማሌኩ ጨዋታ እንደሚደርሱ ተነግሯል፡፡

የዓርብ ውጤት

አል አሃሊ (ግብፅ) 2-2 ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ)

Leave a Reply