ጋቦን ለምታስተናግደው የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሲሸልስ ጋር የሚያደርገው የኢትዮዽያ ብሄራዊ ቡድን በሀዋሳ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ 28 ተጨዋቾችን በመምረጥ በሀዋሳ ከተማ ሴንትራል ሆቴል ማረፊያቸውን አድርገው ከሐምሌ 27 ጀሞሮ ዝግጅታቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን በሀዋሳ ብሄራዊ ስታድየም በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዳቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
በዛሬው የብሄራዊ ቡድኑ የልምምድ ውሎ 24 ተጫዋቾች የተገኙ ሲሆን ተስፋዬ አለባቸው የአሰልጣኙን ፍቃድ አግኝቶ ከቡድኑ ውጪ ሆኗል፡፡ ዲላ የሚገኘው ጌታነህ ከበደን ጨምሮ ሽመልስ በቀለ እና ዋሊድ አታ ደግሞ እስካሁን ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ዝግጅት አልጀመሩም፡፡
ለሁለት በመከፈል ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ጨዋታ የልምምዱ አካል የነበረ ሲሆን በአሰልጣኝ ገብረመድህን የመጀመርያ የብሄራዊ ቡድን ጥሪ የቀረበለት የሲዳማ ቡናው የመስመር አጥቂ አዲስ ግደይ አስደናቂ ብቃቱን አሳይቷል፡፡
ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ አሸንፎ የሌሎችን ውጤት የመጠበቅ ግዴታ ውስጥ በመግባት ጠባብ ዕድል ያለው የኢትዮዽያ ብሄራዊ ቡድን በቅርቡ በካፍ እውቅና ባገኘው የሀዋሳ ስታድየም ነሐሴ 27 ቀን 2008 10:00 ላይ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በተያያዘ ዜና የሀዋሳ ስታድየም መልበሻ ክፍሎች ፣ የጋዜጠኞች ክፍል ፣ የዳኞች ክፍልና ፣ መፀዳጃ ቤቱ ያልተጠናቀቀ ቢሆንም ከጨዋታው ቀን በፊት አጠናቆ ለመጨረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለማየት ችለናል፡፡
በተጨማሪም ሱፐር ስፖርት በሀዋሳ የሚደረጉ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን በቀጥቻ ለማስተላለፍ ከፌዴሬሽኑ ጋር ውል የተፈራረመ ሲሆን ከሲሸልስ ጋር የሚደረገውን ጨዋታም በቀጥታ ያስተላልፋል፡፡